
በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ስኬት በማስቀጠል ከተረጂነት መላቀቅ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ዘርፈ-ብዙ ጸጋዎች ያሏት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል፡፡
እነዚህን ጸጋዎች በሚፈለገው ደረጃ ወደ ልማት መቀየር አለመቻላችን ደግሞ ከተረጅነት እንዳንወጣ አድርጎን ቆይቷል ነው ያሉት፡፡
አሁን ላይም ያሉንን ጸጋዎች በማልማት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት መሸጋገር አለብን በሚል በአገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ዘርፎች ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
አገራዊ ለውጡን ተከትሎም ኢትዮጵያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተቀመጠውን ግብ መሰረት ባደረገ መልኩ በተለይ በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በዚህም በርካታ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰው፤ ይህም ከተረጂነት ለመላቀቅ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባሏት እምቅ የተፈጥሮና ሌሎች ኃብቶች የራሷን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ እንደምትችል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተግባራዊ የተደረጉ ኢኒሼቲቮች ማሳያ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ካሏት ጸጋዎች አንጻር ከተረጂነት ወደ ምርታማነት መሸጋገር እንደምትችል አንስተው በዚህ ረገድ በትብብር መስራት እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡
ተረጂነትን የማስቀረት ሀገራዊ ግብን ለማሳካት በሁሉም ዘርፎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ለዘርፉ እድገት ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን መፍታት ደግሞ ምርትና ምርታማነትን ለመጨምር ከሚሰሩ ስራዎች መካከል አንደኛው መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያን ከተረጂነት አስተሳሰብ ማላቀቅና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ዘመኑ የሚፈልገው አርበኝነት ስለመሆኑም ሚኒስትሩ ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
