




የዞን አስተዳደር ከክልል ጤና እና ኮንስትራክሽን ቢሮዎች ከተገኙ አካላት እንዲሁም ከሆስፒታሉ ኮንትራክተርና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሆስፒታሉ ያለበትን ደረጃ ገምግሟል።
በቦታው ላይ የተገኙት የክልል ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አያለው አደሎ እንደገለፁት የማሻ ሆስፒታል ለብዙ አመታት በተለያዩ ምክንያቶች የዘገየ መሆኑን ጠቁመው በአጭር ግዜ ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችል የክልሉ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝና በዚህም የዋጋ ማሻሻያ ማድረጉን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ ከ16 በላይ የሚሆኑ ብሎኮች በጥሩ ደረጃ ላይ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ችለናል ያሉት አቶ አያለው ያልተጠናቀቁ ጥቃቅን ስራዎችን ተቋራጩ በአጭር ግዜ ውስጥ እንዲያጠናቅቅ ከስምምነት መድረሳቸውንም ተናግረዋል።
ከቀድሞ የደቡብ ክልል ከ27 በላይ ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ተረክበናል ያሉት በክልሉ ጤና ቢሮ የልማት እቅድ ቡድን መሪ አቶ ፍልሞን አልዳዳ ከእነዚህም ውስጥ የማሻ ሆስፒታል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል ።
ሆኖም በአካባቢው ሌላ ሆስፒታል ያለመኖሩን ታሳቢ በማድረግ የክልል መንግስት ልዩ ትኩረት በመስጠት በውል ያልተካተቱ ስራዎች ተካተው እንዲሰሩ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የሆስፒታል ግንባታ ከ95 በመቶ በላይ ተጠናቋል ያሉት የሆስፒታሉ ዋና ኮንትራክተር አቶ በላቸው ነጋሽ በበኩላቸው እስከ አሁን በተለያዩ ምክንያቶች የቆየውን ሆስፒታል እስከ ሀምሌ 15/2016 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ እናስረክባለን ብለዋል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳር አቶ አበበ ማሞ በበኩላቸው ሆስፒታሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት።
የሆስፒታሉ ግንባታ አሁን የተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልፀው እስከ ሀምሌ 15/2016 አመተ ምህረት ባለው ግዜ ውስጥ በኮንትራክተር በኩል የሚታዩ ስራዎች ተጠናቀው እርክክብ እንደሚደረግ ከስምምነት መድረሳቸውን ጠቁመዋል።
ያለቁት ብሎኮች ለስራ ዝግጁ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በሆስፒታሉ የሰው ሀይል ለሟሟላት ቅጥር እየተፈፀመ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
አሁን ላይ የክልል መንግስት ባደረገው ከ3 ሚልዮን ብር በላይ ድጋፍ በሆስታሉ የትራንስፎርመር ተከላ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪ የውሃና መብራት መስመሮች አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ ማረጋገጣቸውን ጠቁመዋል ሲል ማሻ ኤፍኤም ዘግቧል።
