ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ የክልሉን ሲቪል ሰርቪስ መዋቅር ማደራጀት እና ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ላይ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ፐብሊክ ሠርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የሀገራችን ፐብሊክ ሠርቪስ መዋቅርና አደረጃጀት የረጅም ጊዜ ዕድሜ ያለው ነው።ይሁን እንጂ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ውጤታማነትን ያረጋገጠ እና የሲቪል ሠርቫንት አቅም ሊጎልብቱ የሚችሉ አደረጃጀቶች እና ፖሊሲዎች ተቀርጾ ሳይተገበሩ በርካታ ጊዜያትን አስቆጥሯል።
የለውጡ መንግስት የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ሪፎርም መደረግ እንዳለበት በማመን ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት የሠራተኞች አቅም ለመገንባት፣ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ግልጽነትና ተጠያቂነትን መሠረት ያደረገ የሠራተኞች ፍትሃዊ ስብጥር ለመጠበቅ እንዲሁም ነጻና ገለልተኛ የሲቪል ሠርቫንትና ተቋማትን ለማደራጀት ሰፊ ትኩረት የሚሹ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ፐብሊክ ሠርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ክልሉ ከተደራጀ ጀምሮ የክልሉን ሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀትና መዋቅር ለማደራጀትና ለማጠናከር ትኩረት ሰጥተው ሲሰራ መቆየቱን የቢሮ ኃላፊ አቶ አስራት አዳሮ አስታውቀዋል።
በዚህም ክልሉን የሚመስል የክልል ቢሮዎች እና ተጠሪ ተቋማቶችን በማደራጀት በሰው ኃይል ለማሟላት ወደ ስራ መግባቱንም ጠቅሰዋል።
በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም ዞኖች ግልጸንነትና ተጠያቂነትን በጠበቀ አኳኋን የሠራተኛ ስብጥር በጾታ፣ለመደቦች በቂ የትምህርት ዝግጅትና ከቢሮዎች ጋር ትይዩ ያላቸውን ሠራተኞችን ከስድስቱም ዞን በማምጣት የድልድሉ ፍትሃዊነትን በማረጋገጥ ለክልል መንግስት አቅርቦ በማስገምገም ወደ ተግባር ማስገባት መቻላቸውንም ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ክልሉ አዲስ እንደመሆኑ መጠን የክልሉ አመራር በሲቪል ሠርቪስ ዙሪያ በቂ እውቀትና ግንዛቤ ለማሳደግ ከፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የሲቪል ሠርቪስ ፖሊሲ፣ደንብና መመሪያዎች ተዘጋጅተው ለክልል አጠቃላይ አመራሮችና በተዋረድ BPR አዘጋጅ ዳይሬክተሮች ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።
በክልሉ የሚዘጋጀው መዋቅርና አደረጃጀት ከአዲሱ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ከፌደራል ፐብሊክ ሠርቪስ ኮሚሽን ከፍተኛ ባለሙያዎችን በማምጣት ከክልል እስከ ወረዳ ድርስ ያሉ መዋቅሮችን መልሶ ማሻሻያ ጥናት አድርገናል ብለዋል አቶ አስራት አዳሮ።
እንደ አቶ አስራት አዳሮ ገለጻ ከቀድሞ ደቡብ ክልል የመጡ 56 ሺህ 182 መደቦችን መነሻ በማድረግ ከክልሉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ 36 ሺህ 792 መደቦችን ማዘጋጀት ችለናል ብለዋል።
መዋቅርና አደረጃጀት ጥናት እንደገና ማድረግ የክልሉን ኢኮኖሚ እና አሰራር ስርዓቱን ማዕከል ያደረገ ሲቪል ሠርቫንትና መዋቅር ከማደራጀት ባሻገርም ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥን ለመስጠት ጉልህ ሚና ይጫወታል ስሉም ይጠቅሳሉ።
የክልሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን የሚመጥን መደቦችን ማዘጋጀት በመቻሉ አላስፈላጊና በሲቭል ሠርቪስ እውቅና ያልተሰጣቸው መደቦች እንዲስተካከሉና በዚህም በርካታ ይደርሱ የነበሩ ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ወጪዎችን ማትረፍ እንደተቻለም የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል ።
በክልሉ ለፈርጅ ሶስት ከተሞች ዳካ ፥ሺሽንዳ ፥አውራዳ፥ባቹማ፥ቱም፥ ጀሙ፥ ገሳ ፥ጭዳ እና አመያ ከተማዎች አደራጃጀትና መዋቅር ተዘጋጅተው ወርዶ ሥራ ላይ መዋላቸውንም በመጠቆም ።
አቶ አስራት አዳሮ በክልሉ የህግ በላይነት ማስከበር ፈጣን አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽ ማድረግና ብቁ የሰው ኃይል እንዲኖር ማስቻል ሌላኛው የቢሮ ትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም ገልጸዋል።
ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ 24 ሺህ 570 የትምሀርት መረጃዎች ተጣርቶ 2 ሺህ 273 ሀሰተኛ ሆኖ የተገኙ ሲሆኑ በዚህም ሊባክን የነበረ 80 ሚሊየን 54 ሺ ብር ማዳን እንደተቻለም ጠቅሰዋል።
እስካሁን ከ19 ሺህ በላይ ህገወጥ ፋይል ፍተሻ ከተደረገበት መካከል 827 ጉድለት ያለበት ሲሆን በዚህም ከ45 ሚሊየን በላይ ብር ልባክን የነበረውን ማዳን እንደተቻለም ተናግረው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተገኘባቸው 170ቹ አመራሮች ናቸው ብለዋል።
54 ሺህ የመንግስት ሠራተኞች
ማህደር ከደቡብ ክልል ለይተን አጓጉዘው ማምጣታቸውንና ከ4ሺ በላይ ፋይል እስካሁን ማደራጀታቸውን የገለጹት አቶ አስራት 84 ሺህ 450 የክልላችን አጠቃላይ ሠራተኞችን በመለየት ለሚመለከተው አካላት ተላልፏል።
የክልሉ ሠራተኞች መመሪያ እና ደንብ ያካተተ አዋጅ ተዘጋጅተው እንደጸደቀም አቶ አስራት አዳሮ አክለዋል ።
በስራ ወቅት የሚጋጥሙ የመረጃ ጥራትና መረጃዎችን ፈጥኖ ያለማድረስ፣የሰለጠነ የሰው ኃይል ውስንነት፣የበጀት እጥረትና ሌሎች ክፍተቶችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀራረብ እየተሰራ መቆየቱን ገልጸው በክልሉ ስቪል ሠርቪስ ህግ መሠረት በየመስሪያ ቤቶች የመዋቅርና የአደረጃጀት ስራዎችን የሚከታተል ዴስክ ኦዲት ተመድበው ስራዎችን በመከታተል ላይ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ ሠራተኞች የክልሉ መደብ መታወቂያ ቁጥር እንዲኖራቸው ስራዎች ተሠርቷል ያሉ ሲሆን በክልሉ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት፣ ህገወጥ የሰዉ ኃይልን የማሟላት ስራዎች ላይ በተጠናከረ አኳኃን የመከታታል እና ዕርምጃ የመዉሰድ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ስሉም ጠቁመዋል።
የሪፎርም ስራዎችን በሚመለከት በ2017 በሚጀመርባቸው 8 የክልል ቢሮዎች ቅድሜ ዝግጅት ሥራዎች በፖሊስዎችና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም ኃላፈው ጠቅሰዋል።
ረፎርሙ የተደራጀ እና ሁሉን ያካተተ ሀገራዊ እይታና የሲቪል ሠርቪስ እንዲኖር ብሎም የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ እና ፈጣን ለማድረግ ታልሞ እየተንቀሳቀሰ እንዳለም ጨምረው ተናግረዋል።
በፍቅር ከበደ
