



በቤንች ሸኮ ዞን ከዋቻ ማጂ ወደ ሼይቤንች የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የመሬት መንሸራተቶች እየተከሰቱ ይገኛሉ ፡፡
በክልሉ ቤንች ሸኮ ዞን ሰሜን ቤንች ወረዳ ቃሻ ቀበሌ ላይ የተከሰተው የመሬት መንሸራተት ዜጎች እንዲፈናቀሉ ከማድረጉም በላይ በቤንች ሸኮና በምዕራብ ኦሞ ዞኖች የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ጫና እያሳደረ እንደሚገን የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ገልጸዋል ፡፡
አሰተያየታቸውን ከሰጡት ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ከዋቻ ማጂ ወደ ሼይቤንች የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑንና በዕለት ተዕለት የስራ እንቅስቃሴያቸው እንደተስተጓጎለባቸው ተናግረዋል ፡፡
ነዋሪዎቹ በመሬት ናዳ ምክንያት የተጎዳው መንገድ በመንግስት በኩል ጥገና ተደርጎለት የተሟላ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ ሊደረግ ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል ፡፡
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጂማ ቅርንጫፍ ሲኒየር ሰርቬየር የሆኑት አቶ ሀይለመስቀል ዮሐንስ በአካባቢው በተፈጠረ የመሬት መንሸራተት ምክንያት በዋናው መንገድ ላይ በተከሰተው ጉዳት ጊዜያዊ መፍትሔ በመስጠት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል ፡፡
አቶ ሀይለመስቀል ዮሐንስ አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አማራጭ መንገድ ቅየሳ ለማድረግ የአጥኚ ባለሙዎች ቡድን በቦታው ተገኝቶ ተለዋጭ መንገድ ጥናት ማድረጉን ተናግረዋል ፡፡
በታጠቅ አበበ
