





ድጋፉ በካፋ ዞንና በቤንች ሸኮ ዞን በመሬት መንሸራተት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች እንደሚሰጥም ታውቋል።
የሰብዓዊ ድጋፉን ይዘው የቀረቡት የደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ በላይ አሪሶ እንደተናገሩት ግምታቸው ግማሽ ሚሊዮን የሚያወጡ የምግብ እህሎችን ለተጎጂዎች ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ።
ከአቅም በላይ በሆነ የተፈጥሮ አደጋ በመሬት መንሸራተት ሳቢያ የተፈናቀሉ ወገኖችን ባሉበት አካባቢ ቀርቦ በማጽናናት ሰብዓዊነታታቸውን ለመግለጽ ድጋፉ መደረጉንና በቀጣይም ከክልሉ ጎን በመሆን አጋርነታቸውን እንደሚያጠናክሩ አቶ በላይ አሪሶ ተናግረዋል ።
ድጋፉን የተረከቡት የካፋ ዞን ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አክሊሉ አማደ እና የሰሜን ቤንች ወረዳ ግብርና አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ልማት ጽ/ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ የስራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ውቢት ለማ እንደተናገሩት የደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት ወገንተኝነቱን ያሳየበት የወቅቱ ሰብዓዊነት ተግባር ነው ብለዋል።
የተደረገውን ድጋፍ ለተጎጂዎች በፍትሐዊነት ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን ህይወት የመታደግ ስራ ተጠናክሮ ይሰራልም ሲሉም ተናግረዋል ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የግብርናግብኣትና ገጠር ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስራት አሰፋ እንደተናገሩት የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ባስተላለፈው ጥሪ መሰረት የደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት ከሀዋሳ ተነስቶ በክልሉ ችግሩ ባለበት ቦታ ተገኝቶ ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል ።
የደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት የአርሶአደሩን የዘር ዕጥረት በመቅረፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ የሚገኝ ድርጅት መሆኑን በመጥቀስ አልሚ አርሶአደሮች በመሬት ናዳ ምክንያት የተፈናቀሉትን የምርጥ ዘር ድርጅት በመርዳቱ በክልሉ መንግስት ስም አመስግነዋል ።
ተፈናቃይ አርሶአደሮች ዘላቂ በሆነ መንገድ ራሳቸውን እንዲያቋቁሙ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ከተፈናቃይ ወገኖች ጎን በመሆን ዕገዛቸውን እንዲያደርጉ አቶ አስራት አሰፋ ጠይቀዋል።
በታጠቅ አበበ
