







የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2017 ዕቅድ ውይይት በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አማካሪና የጽ/ቤት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዮሀንስ መላኩ እንደገለፁት በክልሉ የምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ምርታማነትን ለማረጋገጥና በምግብ ራስ ለማስቻል በሚሰራው ሥራ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
ግብርና ከማምረት በላይ በመሆኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በ10 አመት ውስጥ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እና ለዜጎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በምግብ ስርዓት ፕሮግራም የተጀመሩ ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የግብርና ልማት ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግና ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የአርሶ አደሩንና የባለሙያውን አቅም ለማሳደግ ትኩረት ተደርጎ በመሰራቱ ለውጦች እየመጡ መሆኑንም አንስተዋል።
ፕሮግራሙ በ2016 በጀት አመት በክልል በርካታ ድጋፎችን በማድረግ ማህበረሰቡ በምግብ እራሱን እንዲችል ለማስቻል በርካታ ስራዎችን ማከናወኑ ገልፀው በአንድ አንድ አከባቢዎች የህዝብ ጥያቄ የነበሩ ትልልቅ የመስኖ አውታሮችን በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡ አስችሏልም ብለዋል።
በ2016 የተመዘገቡ ውጤቶችን ለቀጣይ እንደ ግብአት በመውሰድ በ2017 ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ የፕሮግራሙ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ወንድወሰን ሁሴን በበኩላቸው በክልሉ በሁሉም መዋቅሮች በተሰራው ስራ በሀገር ደረጃ ሶስተኛ ደረጃ መውጣት መቻሉን ገልፀው ለዚህም ለመጣው ውጤት ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።
በመጣው ውጤት መዘናጋት አያስፈልግም ያሉት አቶ ወንደሰን በቀጣይ 2017 የተሻለ ተግባር በመፈፀም ከዚህ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቃል ብለዋል።
መድረኩ በ2016 በጀት አመት የወረዳዎችንና የፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ዕቅድ በመገምገምና ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል ጉድለቶችን ለይቶ የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ በቀጣይ በጀት አመት ትምህርት የምሚወሰድበት መድረክ መሆኑን አንስተዋል።
በ2017 በጀት አመት ዕቅድ ለመፈፀም የሚያስችሉ ስልቶችን ለመንደፍና አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መድረክ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል።
በመድረኩም የፕሮግራሙ ወረዳ ፈፃሚዎችና የክልሉ የሥርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን የቤንች ሸኮ ዞን ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
