
REDD+Investment program (የ’ሬድ ፕላስ እንቨስትመንት ፕሮግራም) ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ ሀገሮች ከደን መመንጠርና መመናመን ጋር በተያያዘ ካባቢ አየር የሚለቀቀውን ሙቀት አማቂ ጋዝ ለመቀነስ እንዲሁም በደን ውስጥ የካርበን ክምችትን ለመጨመር በአለም ዓቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ የተዘረጋ የፖሊሲ አግባብ እና ውጤት ተኮር ማትጊያ ስርዓት ነው።
ፕሮግራሙ በዋናነት በደን አጠባበቅና ልማት እንዲሁም በህብረተሰብ ኑሮ ማሻሻል ላይ በኖርዌይ መንግስት ገንዘብ ድጋፍ የሚሠራ መንግስታዊ ያልሆነ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም ነው።
ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ በ’ሬድ ፕላስ እንቨስትመንት ፕሮግራም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚከናወኑ ተግባራት ከአንድ መቶ 12ሺህ በላይ ማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ደን፣አከባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ የሬድ ፕላስ እንቨስትመንት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር የሪቾ ብርሃኑ ተናግረዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የሬድ ፕላስ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም በአምስት ክላስተሮችና በፕሮግራሙ በታቀፉ በ29 ወረዳዎች መጠነ ሰፊ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ፕሮገራሙ በሚተገበርባቸው ዞን ወይም ወረዳዎች የደን መጨፍጨፍ እና መመናመን እንድከሰት የሚያደርጉ ችግሮችን በመለየት የተስተካከለ አየር ንብረት እንዲሰፍን እንዲሁም የዘላቂ ደን አያያዝ እንዲረጋገጥ በትኩረት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
የክልሉ የ’ሬድ ፕላስ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር የሪቾ ብርሃኑ እንደተናገሩት ፕሮግራሙ በተለይም በዘላቂ ደን አያያዝ/አሳታፊ የደን አስተዳደር ማቋቋም፣ጣዉላ ነክ ያልሆኑ የደን ዉጤቶችን ከደን ዉስጥ በህጋዊ መንገድ በዕቅድ አንድያለሙና እንዲጠቀሙ ማድረግና ኑሮን በደኑ ያደረጉ ማህበረሰብ ክፍሎችን በቅድሚያ ልየታ በማድረግ በኑሮ ማሻሻያ ተጠቃሚ እንድሆኑ የማድረግ ተግባራት ላይ ትኩረት በመሰጠት እየሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ በፕሮግራሙ በታቀፉ 29 ወረዳዎች በዘላቂ የደን አያያዝ /አሳታፊ የደን አስተዳደር በማቋቋም ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠርና በማሳተፍ የተፈጥሮ ደን በመከለል በደኑ ላይ የሚደርሱ ችግሮችን በመለየት ዕቅድ በማዘጋጀት የልማት፤የጥበቃ፤የአጠቃቀምና የክትትል ስርዓት በመዘርጋት ከህገወጥ አጠቃቀም ወደ ህጋዊ በማምጣት የደን ዉድመትን በመቀነስ እንዲሁም የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸዉን የደን ችግኞችን በተጎዱ እና በተለዩ ቦታዎች ተከላ የማካሄድ ስራዎች ተሰርተዋል፣ እየተሰራም ይገኛል ብለዋል ዶክተር የሪቾ ብርሃኑ፡፡
እስካሁን በዘላቂ ደን አያያዝ 393 ሺህ ሄክታር የተፈጥሮ ደን በመከለል 37 ሺህ 202 የማህበሩ አባላትን በመያዝ 241 የአሳታፊ ደን አስተዳደር ማህበራትን በማቋቋም ህጋዊ ሰዉነት ማግኘቱንም ጠቅሰዋል።
ኑሮን በደኑ ያደረጉ ማህበረሰብ ክፍሎችን በቅድሚያ ልየታ በማድረግ በኑሮ ማሻሻያ ተጠቃሚ እንድሆኑ መደረጉንም አስተባባሪው ጠቁመዋል።
በዚህም ችግኝ ጣቢያ በማቋቋም ለወጣቶችና ለሴቶች የስራ ዕድል መፈጠር ፤በጓሮ አትክልት ልማት፤ ደን ጥምር እርሻ ስራ፤ የበግና ፍየል ማሞከትና እርባታ ስራ፤ የንብ ማነብ ስራ፤ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፤ የተሻሻሉ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ማምረትና ስርጭት እንዲሁም ዝቅተኛ መጠን ያላቸው የሶላር ኃይል በማቅረብ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም ገልጸዋል።
እስካሁን ድረስ በፕሮገራሙ ቀርበው 405 ሚሊዮን 667 ሺህ 731 ብር ስራ ላይ መዋሉን ያብራሩት ዶክተር የሪቾ ብርሃኑ በዚህም ከአንድ መቶ 12 ሺህ በላይ ማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሆናቸውም ተናግረዋል።
የተፈጥሮ ደን ያለባቸው ቀበሌዎችን በመለየት በፕሮገራሙ የታቀፉ ወረዳዎች የአሳታፊ ደን አስተዳደር ማህበራት እንድመሰረቱ ማድረግና በደኑ ላይ ኑሮን መሠረት ያደረጉ የማህበረሰብ ክፍሎችን በፕሮግራሙ በሚቀርቡ በኑሮ ማሻሻያ ተጠቃሚ እንድሆኑ ማድረግ እንዲሁም በደን ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ወይም አደጋዎችን እንድከላከሉ ማድረግ የፕሮግራሙ የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች እንዲሆናቸውም ዶክተር የሪቾ ብርሃኑ አብራርተዋል ፡፡
ከደኑ የሚገኘዉን የካርበን ሽያጭ ለማምጣት ቅድመ ዝግጅትና መሰረታዊ መረጃዎችን ከሚመለከታቸው ጋር የማሰባሰብና የማደራጀት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ዶክተሩ በማከል።
ምንም እንኳን ፕሮግራሙ በክልሉ አምስት ክላስተሮችና 29 ወረዳዎቸን ይዞ እየሰራ ብገኝም ሌሎች ያልተካተቱ የደን አቅም ያላቸው አካባቢዎችን በነባር የተያዙ ወረዳዎች ጎን ለጎን የጋራ ትስስር በመፍጠር በቀበሌዎች ማህበራት ተደራጅተው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ሲሉም ዶክተሩ አስረድተዋል፡፡
ሀገረዊ አጀንዳ የሆነውን የአረንጓደ አሻራ መርሃ ግብር ከመደገፍ አንጻር በፕሮግራሙ የሚደራጂ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የደን እና የፍራፍሬ ችግኞችን በማዘጋጀት በወል ቦታ፡ በግል ማሳ፡ በተቋማት እና የተጎዱ ቦታዎች ተለይተው ችግኞች እየተተከሉ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ይህም መንግስት እያስፈጸመ ያለዉን የአረንጓዴ አሻራን የሚያበረታታና የተከላው ጽድቀት ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፕሮግራሙ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ለማሳካት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን እያቀረበ ይገኛል፡፡ ይህንን ተግባር ፕሮግራሙ በዘላቂነት አጠናክረው ይቀጥላልም ብለዋል፡፡
የደን ሀብቶችን በዘላቂነት መጠበቅ፤ መጠቀምና ማልማት፤ የተጎዱ ቦታዎችን በደን ማገገም፤ ጣዉላ ነክ ያልሆኑ የደን ዉጤቶችን ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ከሀብቱ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ስነምህዳራዊ ጥቅሞችን ለማግኘት እና የአየር ንብረት ለዉጥን ተጽዕኖ ለመቋቋም ለአለም አቀፍ ልማት አስተዋጽኦ ማድረግ የፕሮግራሙ የቀጣይ ተልዕኮ እንደሆነም ዶክተር የሪቾ ብርሃኑ ጨምረው አስረድተዋል።
