በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከ355 በላይ ሄክታር ቢኤች140 የበቆሎ ምርጥ ዘር እያለማ እንደሚገኝ የደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት አስታወቀ

Spread the love

እየለማ ያለው የምርጥ ዘር ብዜት ስራ እየተስተዋለ የሚገኘውን የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑም ተመላክቷል ።

የደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት የማኔጅመንት አካላት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እየለማ የሚገኘውን የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት ስራ ተዘዋውረው ተመልክተዋል ።

በምልከታው ላይ የተገኙት የደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በላይ ሀሪሶ እንደተናገሩት ድርጅቱ የተለያዩ የምርጥ ዘር ብዜት ስራዎችን በአራት ክልሎች ከ4 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ እያለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

ከአራቱ ክልሎች አንዱ በሆነው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከ355 ሄክታር በላይ ቢኤች 140 የበቆሎ ምርጥ ዘር መልማቱን ተናግረዋል ።

የምርጥ ዘር ብዜቱ በክልሉ በምዕራብ ኦሞ ዞን በስምንት አልሚ ባለሀብቶች ውል በመግባት እየተባዛ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ በላይ ሀሪሶ ሰብሉ በአሁኑ ሰአት በተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል ።

በአልሚ ባለሃብቱ እየለማ የሚገኘው ይህ የበቆሎ ምርጥ ዘር አሁን ላይ የሚስተዋለውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ዕጥረት ለመቅረፍ ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል ።

በደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት የዘር ብዜትና ጥራት ማረጋገጥ ክፍል ሃላፊ የሆኑት አቶ በላይነህ ዘውዴ በሰጡት አስተያየትም የምርጥ ዘር ብዜቱ ለአካባቢው ተወላጆች የስራ ዕድል መፍጠርና የቴክኖሎጂ አሰራሮችን እንዲያውቁ አስችሏል ሲሉም ተናግረዋል ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓት አቅርቦት የስራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ማሞ በለጠም በምልከታ ወቅት በሰጡት አስተያየት የደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት በክልሉ የሚስተዋለውን የአርሶ አርብቶ አደሩን የዘር አቅርቦት ፍላጎት ክፍተት ለመሙላት በብዛትና በጥራት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

አቶ ማሞ አክለውም እየተከናወነ ያለው የምርጥ ዘር ብዜት ተስፋ ሰጪና የተሻለ ምርት የሚገኝበትም ነው ሲሉ ተናግረዋል ።

የክልሉ ግብርና ቢሮም ከደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት ጋር በመቀናጀት የክህሎትና የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍ በቅንጀት ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል ።

በምርጥ ዘር ብዜት ከተሰማሩ 8 ባለሃብቶች መካከል አቶ ብርሃኑ አለባቸው ከጀግናው ብርሃኑ ምርጥ ዘር ልማት ድርጅት፣ አቶ ሰንበት ዱር ከበላይነህ ክንዴ ይርት ሸለቆ ጥምር እርሻ እንዲሁም አቶ አብይ አቦነህ ከኦሞ ቪው ጥምር እርሻ ልማት በሰጡት አስተያየት ከደቡብ ምርጥ ዘር ድርጅት ጋር ውል በመግባት ቢኤች140 የበቆሎ ሰብል ምርጥ ዘር ብዜት እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በሰብሉ ቡቃያ ወቅት ለሁለት ወራት የሚጠጋ ፀሀይ በመብዛቱ በምርት ወቅት ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ስጋት እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል ።

ይሁን እንጂ ጠንክረው የእርሻ ስራውን በማስቀጠል እየለማ ያለው የበቆሎ ምርጥ ዘር ችግሮችን የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ በአሁን ወቅት ሰብሉ በተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኝና የተሻለ ምርትም እንደሚያገኙ ገልፀዋል ።

ባለሃብቶቹ እያከናወኑት ባለው የእርሻ ልማት ስራ ለአካባቢው ተወላጆች ቴክኖሎጂን የማስረጽና የስራ ዕድል ለዜጎች በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ እንደ ቻሉም ተናግረዋል ።

ወጣት ቸንበሩ ዕድሉ በጀግናው ብርሃኑ የምርጥ ዘር ብዜት እርሻ ውስጥ ተቀጥሮ በመስራቱ የተሻለ ዕውቀት እንደቀሰመና በሚያገኘው ገቢ ተጠቃሚ መሆኑንም ተናግሯል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምዕራብ ኦሞ ዞን የሚለማው የቢኤች 140 ምርጥ ዘር በቆሎ ተመራጭና ውጤታ ሲሆን ከ355 ሄክታር ውስጥ 348ቱ የተመሰከረለትና 7ሄክታሩ መስራች ዘር ሆኖ እየለማ ይገኛል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *