
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካኝነት ለአየር ንብረት ለውጥ መዛባት ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠች እንደምትገኝ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡
ሚኒስትሯ ከተቋሙ የስራ ባልደረቦች፣ ከጀኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ሰራተኞችና ከዘንድሮ የኮሌጁ ተመራቂ ተማሪዎች ጋር በመሆን በጀኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ግቢ ተገኝተው አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት፤ የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት የወቅቱ የዓለማችን የስጋት ምንጭ ሆኖ ይገኛል ብለዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት የሰው ልጆችንና አጠቃላይ ህይወት ያላቸው ነገሮችን ህልውና ስጋት ላይ ጥሎት እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
ለዚህ አደጋ የተቀናጀና አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ካልተቻለ አዳጋው የከፋ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ይህን የህልውና አደጋ ቀድማ በመገንዘብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄን በይፋ መጀመሯን አስታውሰዋል፡፡
መርሃ ግብሩም አሁን ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስትርም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ንቁ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱንና አሁንም እያደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
የተቋሙ ሰራተኞች በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሃ ግብር ላይ ለመሳተፍ ዝግጅት ማድረጋቸውንም እንዲሁ፡፡
ሁሉም ዜጋ በነቂስ ወጥቶ በመርሃ ግብሩ እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጀኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን መለሰ ይግዛው በበኩላቸው፤ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች በኮሌጁ ግቢ ተገኝተው ችግኝ በመትከላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
ኮሌጁ በቀጣይም የተተከሉ ችግኞችን መንካባከብ ላይ በስፋት ተሳትፎ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
