



ኢትዮጵያ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) አባል ሀገራትን በሃይል አቅርቦት ለማስተሳሰር በሚደረገው ርብርብ የላቀ ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን የነዳጂና ኢነርጂ ባለስልጣን ገለጸ፡፡
የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) አባል ሀገራትን በኤሌክትሪክ ሃይል ለማስተሳሰር በተደረጉ የጥናት ግኝቶች ዙሪያ በአዲስ አበባ አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው።
በአውደ ጥናቱ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአባል ሀገራት ተወካዮችና የተለያዩ ባለደርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የኤሌክትሪሲቲ ዘርፍ ቁጥጥር ቴክኒካል ዳይሬክተር ባህሩ ኦልጅራ፤ የኮሜሳ አባል ሀገራትን በኤሌክትሪክ ሃይል ለማስተሳሰር የህግ ማዕቀፎች፣ የታሪፍ ሁኔታና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የአሁኑ አውደ ጥናት ዓላማም የኮሜሳ አባል ሀገራትን በኤሌክትሪክ ሃይል ለማስተሳሰር የሚያስችል የጋራ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግን ያለመ ነው ብለዋል።
የኅይል ግብይት፣ ቁጥጥርና አስተዳደር የሚመራበትን ማዕቀፍ ለማዘጋጀት የተቋቋመው የጥናት ቡድን በአባል ሀገራቱ ባደረገው ጥናት ያገኘው ውጤት ይፋ የሚደረግበት መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የጥናት ቡድኑ ባቀረበው ውጤት ላይ አባል ሀገራቱ የመጨረሻ አስተያየት ከሰጡበት በኋላም የጋራ ታሪፍና ህግ ወጥቶለት ገቢራዊ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ከኮሜሳ አባል ሀገራት የተሻለ የኅይል ምንጭ መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ አገራቱን በኅይል ለማስተሳሰር በሚደረገው ጥረት የላቀ ሚና እየተወጣች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የምስራቃዊ አፍሪካ የኅይል ልማት ዘርፍ ዋና ጸሃፊ ጀምስ ዋሆጎ፤ በአንድ አገር ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
አፍሪካ በቂ የኅይል አማራጭ ቢኖራትም በመሰረተ ልማት እጥረት እንዲሁም በአገራት ቅንጅት ጉድለት እስካሁን በአግባቡ እርስ በርስ መተሳሰር አለመቻላቸውን ጠቅሰው ቀጣይ ብዙ መሰራት እንዳለበትም አመላክተዋል።
ለዚህም ለኅይል ልማትና ትስስር የሚያገለግል የህግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው አውደ ጥናት ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቀጥል መሆኑ ታውቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
