


















ፕሮግራሙ በሚክረቾ አባላት ባህላዊ የምርቃት ስነስርዓት በማድረግ በይፋ ነው የተከበረው።
በዘመን መለወጫ ስነስርዓት ላይበመገኘት ንግግር ያደረጉት የአንድራቻ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አየለ አንገሎ የሸካቾ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ማሽቃሬ ባሮ ” ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በማልማትና በመንከባከብ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ የአሁኑ ትውልድ ትልቅ አደራ ያለበት ነው ብለዋል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ ዞኑ የኤክስፖርት ምርቶች በስፋት የሚመረቱበት፣ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ የሸካ ደን ባዮስፌር መገኛ አካባቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል ።
የሸካቾ ባህላዊ የአስተዳደር መዋቅር ሙሉዕነት ጎድሎት ለዘመናት ተረስቶ የቆየ በብልጽግና መንግስት ሙሉዕነቱ ተመልሶ ዳግም ወደ ስራ በመግባቱ በርካታ ተግባራት በመከናወናቸው በዞኑ ለውጦች መምጣት መቻሉን ተናግረዋል ።
የሸካቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ማሽቃሬ ባሮ ” የአዲስ ተስፋ ውልደት፣የፊትን በተስፋ የሚጠብቁበት፣የተጣላ የሚታረቅበት ፣በአንድነት ለአንድነት የሚከበር በዓል ነው ሲሉም ተናግረዋል ።
የክረም እርሻ የዘር ወቅት ተጠናቅቆ ከዝናብ ወደ ብርሃን የምንሸጋገርበት የአደባባይ ባህልም ነው ሲሉ አቶ አበበ ተናግረዋል ።
የሸካቾ ባህላዊ የአስተዳደር መዋቅር ከሚክረቾ እስከ ገቢታቶ ያሉ ወራፎዎች በዓመቱ ያከናወኑት ስራዎች የሚገመገምበት ፣ በሌላ በኩልም እያንዳንዱ የሚክረቾ አባል በጥንካሬ የፈጸሙት የሚበረታቱበት፣ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳዩ የሚወቀሱበት ፣ለቀጣይም ስራ አዋጅ የሚታወጅበት እንደሆነም ተናግረዋል።
የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ ባስተላለፉት መልዕክት የሸካቾ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ማሽቃሬ ባሮ” በክልሉ ከሚገኙ ቱባ ባህሎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
የህዝቦችን ትስስር ፣አንድነት፣ ህብረብሔራዊነትን በማጎልበት ረገድ ባህል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አቶ ፋንታሁን ተናግረዋል ።
ባህልን ማልማት፣መንከባከብ ፣መጠበቅ፣ የህዝቦች ትልቅ የማዕዘን ድንጋይ፣መነሻ ታሪካቸውን የሚያዩበት መነጽር፣ ዘላቂ ልማትና ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል ወሳኝ እሴት ነው ሲሉም ተናግረዋል ።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ብዝሃነትን ለማስቀጠል ጠንካራ ባህል መገንባት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል ።
ባህልን ማልማትና መንከባከብ ለህብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ትልቅ እሴት መሆኑንም አቶ አልማው ተናግረዋል ።
ዞኑ በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎች ያሉት አካባቢ መሆኑንና የሸካቾ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ “ማሽቃሬ ባሮ ” አንዱ ማሳያም ነው ብለዋል።
ይህ ባህል ለምቶ ጥቅም ላይ እንዲውልም የአካባቢው ተወላጆች የበለጠ በማልማት ለማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል ።
የሸካቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ማሽቃሬ ባሮ” በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በድምቀት እየተከበረ ነው ።
የፖሊስ ሰራዊት አባላት ወታደራዊ ትዕይንት ፣ የዞኑ ባህላዊ ኪነት ጭፈራ፣ የፈረስ ጉግስ ፣ ዩቦ የተሰኘው ታላላቅ ኹነቶች ሲፈጠሩ የሚደረግ በጦርና ጋሻ በተዋበ የባህል አልባሳት “ታላላቆች ይኑሩልን” በሚል ዜማ በማሰማት በዓሉ በድምቀት እየተከበረ ነው።
የሸካቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ “ማሽቃሬ ባሮ” በ17ኛው የሸካቾ ንጉስ በሆኑት ታቶ ተቺ ቄጆቺ “ነግረቶ” ተጎስሞ ተግባር ላይ የሚውሉ አዋጆች ቀርበው ህብረሰቡ በመቀበልና ስራ ላይ እንዲያውለው በማሳሰብ ፕሮግራሙ ተቋጭቷል።
በታጠቅ አበበ
