2016 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ዓመት ነበር፦ የምጣኔ ሀብት ባለሞያ

Spread the love

2016 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ዓመት ነበር ሲሉ የፖሊሲ አማካሪ እና የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) ገለፁ።

በበጀት ዓመቱ 8.16 በመቶ የነበረውን አጠቃላይ ሀገራዊ የምጣኔ ሀብት ዕድገት በቀጣይ ወደ 8.4 በመቶ ለማሳደግ መታቀዱንም ባለሞያው በተለይ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።

በወጪ ንግድ ዘርፍም ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ጠቅሰዋል።

በ8.16 በመቶ ቀርቶ በ5 በመቶ እንኳ የሚያድጉ ሀገራት በዓለም ላይ ጥቂት ስለመሆናቸው የጠቆሙት የምጣኔ ሀብት ባለሞያው፤ አውሮፓውያኑ እና ቻይና እንኳ በዚህ ልክ አለማደጋቸውን ጠቅሰዋል።

በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ለዳያስፖራው ጭምር ትልቅ አቅም የፈጠረ ስለመሆኑም አንስተዋል።

መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎች በቀጣይ ዓመታት ለሚመዘገበው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም አመላክተዋል።

በከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ አበረታች ዕድገት ስለመኖሩ አንስተው፤ በቀጣይ ዓመታት በህብረተሰቡ አኗኗር ላይ ለውጥ ለማምጣት መስራት ይገባል ብለዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት መምህር እና ተመራማሪው በዓሉ ጡቄሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በተያዘው 2017 በጀት ዓመት ኤክስፖርት መር ኢኮኖሚን ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ይህም አምራቹን ማህበረሰብ በማበረታታት የኤክስፖርት ምርቶች እንዲበራከቱ ያስችላል ብለዋል።

ቁጠባን ማበረታታት፣ ግብርናን ማስፋት ያስፈልጋል የሚሉት መምህሩ፤ ምርታማነትንም ማሳደግ እንደሚገባል ይመክራሉ።

የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችም ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው በመሆኑ በቀጣይ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሀገራዊ ሰላምና እና ደህንነትን በማረጋገጥ ለቀጣይ የተያዙ የኢኮኖሚ ግቦችን ለማሳካት መስራት እንደሚገባ የጠቆሙት ምሁራኑ፤ የዜጎችን ገቢ እና ምርታማነትን በማሳደግ የዋጋ ግሽበትን ማረጋጋት እንደሚያስፈልግም ማመልከታቸዉን ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *