ኢትዮ-ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይና ሲምፖዚየም ቅድመ ሁነት ተካሄደ

Spread the love

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ኢትዮ- ግሪን ሞቢሊቲ 2024 በሚል ስያሜ በመጪዉ ህዳር ወር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ታላቅ ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይና ሲምፖዚየም ያካሂዳል።

የቅድመ ሁነት ፕሮግራሙ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው የኢምባሲ ተወካዮች፣ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰሩ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የዘርፉ ባለሃብቶች እና ጥሪ ተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ትናንት መሰከረም 28/2017 ዓ.ም አመሻሽ በስካይላይት ሆቴል ተካሂዷል፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶ/ር ዓለሙ ስሜ መርሃ ግብሩን በንግግር በከፈቱበት ወቅት በኢትዮጵያ በተለይም ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ መንግስት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ መሰረተ ልማት፣ በከተማ ትራንስፖርት እና አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ዘላቂ የትራንስፖርት ስርዓት ለመዘርጋት በቁርጠኝነት እየሰራች ትገኛለች ብለዋል፡፡

በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍም ይህንን ለመደገፍ ታዳሽ የኃይል ምንጭ የሚጠቀሙ ተሸከርካሪዎችን በማስፋትና ዘርፉን በማበረታታት ከተሽከርካሪ የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ በመቀነስ ሀገራዊ ዓላማውን ለማሳካት የሚጠበቅብንን ለመወጣት እየሰራን ነው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሀገራችን በማስገባት የበካይ ጋዝ ልቀትንና የሃይል ብክነትን ለመቀነስ ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ተጀመረውና በሌሎች ከተሞችም እየተስፋፋ ያለው የኮሪደር ልማት ለአረንጓዴ ትራንስፖርት የሚኖረው አስተዋፅኦ የጎላ እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ዘላቂ አረንጓዴ ትራንስፖርት ግንባታን እውን ለማድረግ በመንግስት ብቻ የሚሰሩ ስራዎች በቂ ስለማይሆኑ የግል ባለሃብቱ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በዚህም አረንጓዴ ትራንስፖርት ለሀገራችን አዲስ ከመሆኑ የተነሳ አምራችና ተጠቃሚውን የህብረተሰብ ክፍል በማገናኘት የሚስተዋለውን ብዥታ ማጥራትና ግንዛቤን ማሳደግ አስፈላጊ በመሆኑ ይህ አውደርዕይና ሲምፖዚየም መዘጋጀቱን መናገራቸውን ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

ከዚህ ሲምፖዚየም ጎን ለጎንም የአፍሪካ ሀገራት ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ሀላፊዎች የሚሳተፉበት ተጓዳኝ የምክክር መድረክ (PIDA Week) ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

በሲምፖዚየሙ አምራች ኩባንያዎች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም ከመላው አፍሪካ የሚገኙ 700 በላይ ተሳታዎች እንደሚሳተፋበት ገልፀዋል፡፡

ሲምፖዚየሙ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም በዘርፉ ለሚኖረው መነቃቃትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንዳለው የጠቆሙት ሚኒስተሩ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ የስራ እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ለኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ሲምፖዝየም ቅድመ ሁነት ላይ የተጋበዙ አካላት ሲምፖዚየሙን እውን ለማድረግ አብረው ለመስራትና በገንዘብም ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *