በምዕራብ ኦሞ ዞን “የፀጥታ ችግሮች በመፍታት በቀጠናው ዘላቂ ሠላም የማስፈን ውጥን”

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምዕራብ ኦሞ ዞን የሚገኙ ነዋሪዎች አርብቶ አደርና ከፊል አርሶአደርነት ህይወታቸውን ይመራሉ፡፡ በክልሉም ሆነ በዞኑ ባለፉት ጊዜያት በተከሰቱ የእርስ በርስ ግጭቶች ምክንያት በህብረተሰቡ የተረጋጋ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል፡፡

ለዚህም በዞኑ በሱርማ፣ በቤሮና በማጅ አካባቢዎች የሚስተዋለውን የፀጥታ ችግር በመፍታት ዘላቂ ሠላም ማስፈን ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ፀጥታን የማረጋጋጥና ህግ ማስከበር ተግባራት እየተከናወኑ ቆይተዋል፡፡ ሠላምን ለማስፈን ከህዝብ ጋር በመሆን በተሰራው ተከታታይ ስራ አሁን ላይ አንፃራዊ ሠላም ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

በምዕራብ ኦሞ ዞን በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አካባቢ የሚከሰቱትን ግጭቶች በመፍታት ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ በተሰራው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ በተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን የዞኑ ሠላምና ፀጥታ ሚሊሸ መምሪያ ኃላፊ አቶ ባህሩ ቡርጂ ተናግረዋል፡፡

በዞኑን ሠላምና ፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ዞን አቀፍ የሠላምና መረጋጋት መድረክ ከመጋቢት 2014 ዓ.ም ጀምሮ በተደጋጋሚ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡

መድረኩ በዋናነት ቀደም ሲል በአርብቶ አደር አካባቢ ተቋርጦ የነበረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን መልሶ ለማገናኘት ከዞን ማዕከል ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በትኩረት መሰራቱን የመምሪያ ኃላፊ አቶ ባህሩ ገልፀዋል፡፡

በዞኑ ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር የእርስ በእርስ ግጭት ፣የከብት እና የተለያዩ የስርቆት ወንጀሎች የህዝብን ሠላምና ደህንነት ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግሮችን ሲያደርሱ ቆይተዋል ነው ያሉት።

በአርብቶ አደር አካባቢ ከሚስተዋሉ የሠላምና ፀጥታ ችግሮች ዋናኘው በዞኑ በሚገኙ አራቱ ብሔረሰቦች መካከል የሚፈጠረው የእርስ በእርስ ግጭት ነው ያሉት ኃላፊው ግጭቱ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ እንደነበረም አንስተዋል ፡፡

በወቅቱም በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ለፀጥታ መንስዔ ተብሎ በተለዩ የጥሎሽ መብዛት፣ የአስካሪ መጠጥ ዝውውር ፣ የአሻ(የደም ካሳ)ጉዳዮች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን የፀጥታ መዋቅሩን የመፈተሽ እና በአዲስ መልክ የማደራጀት ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።

ህዝቡን ሠላማዊ በማድረግ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተደረገው ጥረት ሁሉም አካባቢዎች የማህበረሰብ እርቀ-ሠላም በመፈፀም በዞኑ ህዝቦች መካከል ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረውን ግንኙነት መልሶ በመገንባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሮችን መለየት መቻሉን አቶ ባሀሩ ገልፀዋል።

የውስጥ ችግሮችን በጋራ በመፍታት አመራሩና የፀጥታ አካላት በሠላም ጉዳይ ቅንጅታዊ አሠራርና የጋራ መግባባትን ፈጥረው
በከፍተኛ ጫና ውስጥ ወድቆ የነበረውን የዞኑን ሠላም ለማረጋገጥ በየደረጃው ባሉ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና የፀጥታ መዋቅር ጋር በርካታ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውንና በዚህም “የዞኑን ሠላም ለመስፈን በተሰራው ሥራ የፀጥታ ችግሮችን ከመቅረፍ አልፎ አንፃራዊ ሠላም ማረጋገጥ ተችሏል” ብለዋል፡፡

የመጣውን ሠላም ዘላቂ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ባህሩ የህግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያም ጠንካራ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንና ከዚህ በፊት ወንጀል ሰርተው የተደበቁ ግለሰቦችን ለህግ የማቅረብ፣ በግጭት ወቅት የተዘረፉ ከብቶችን ለባለቤቶቹ የመመለስ እና በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ አካላት የመለየት ስራ መከናወኑን አብራርተዋል፡፡

በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የማህበረሰብ ትስስር እንዲጠናከር እና በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጦ የነበረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወደቀደመ አቋሙ እንዲመለስ ዞኑ ከአጎራባች ዞኖች እና ከጋምቤላ ክልል መካከልም ያለውን የፀጥታ ችግር በመፍታት የህዝቦች አብሮነትና ሰላም መመለስ የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የግጭት መፍቻ ስርዓት መከተል፣የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማጠናከር፣ከአጎራባች ክልሎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር፣የአብሮነት እና የመከባበር እሴቶችን በማጎልበት ተችሏል ነው ያሉት

ባለፉት ዓመታት የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለማረጋጋትና አሁን ለታየው ዘላቂ ሠላም ዞንና በስሩ የሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ያበረከቱት አስተዋፅኦ ቀላል የማይባል አይደለም ብለዋል።

አሁን በዞኑ የመጣውን አንፃራዊ ሠላም ቀጣይነት እንዲኖረው እና ወደ ዘላቂ ሠላም ለማሸጋገር የተጀመረው ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ አጠናክሮ ለማስቀጠል ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል

በዞኑ በመኤኒት ብሔረሰብ ዘንድ እየተተገበረ ያለው ለሟች ቤተሰብ የሚደረገው የአሻ ስርዓት ለፀጥታው ችግር መንስኤ በመሆኑ ህገ ደንብ በማውጣት እና በማጽደቅ ተግባራዊ እንዲሆን ተደርጓል ያሉት ኃላፊው በተጨማሪም የጥሎሽ ከብት አከፋፈል ስርዓት ወጥ ማድረግ፣ የእርስ በርስ ግንኙነት የግብይት ሂዳቱን ማጠንከር እና ህገወጥ የጦር መሣሪያዎች ቁጥጥር ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራም አብራርተዋል ፡፡

ዞኑ ለፀጥታው ተግባር በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ስራውን በተሻለ መንገድ እያከናወነ እንደሚገኝና የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ መዋቅር ተግባሩን እየደገፈ መሆኑን አቶ ባህሩ ገልፀዋል፡፡

ከአጎራባች ዞኖች እና ከጋምቤላ ክልል መካከልም ያለውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት በመፍታት የህዝቦች አብሮነትና ሰላምን መመለስ የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎች የሚከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አሁን በምዕራብ ኦሞ ዞን የመጠውን አንፃራዊ ሠላም ዘላቂ ለማድረግ የሁሉም አካላት እገዛ እና ትብብር የሚፈልግ ነው ያሉት አቶ ባህሩ ቡርጂ መላው የዞኑ ህብረተሰብ የፀጥታ መዋቅርን በመደገፍ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *