


የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ትምህርት ቢሮ ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ በተገኘ ድጋፍ በዩኒሴፍ ፕሮጀክት ከታቀፉ 14 ወረዳዎች ጋር በትምህርት ዙሪያ የማህበረሰብ የባህሪ ለውጥ ላይ በሚዛን አማን ወይይት ተካሂዷል ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤት መሻሻል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ አጊቶ እንደገለፁት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ያለመምጣት ፣ ማቋረጥ እንዲሁም ባሉበት ክፍል መድገምን በክልሉ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ በማህበረሰቡ ዘንድ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል ።
አቶ ፍቃዱ አክለውም ዩኒሴፍ ኢትዮጽያ በትምህርት ላይ የሚሰራው ስራ አጋዥ በመሆኑ ከመደበኛ የትምህርት ስራ ጋር በማስተባበር የተሻለ ለውጥ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።
በክልሉ ትምህርት ቢሮ የዩኒሴፍ አስተባባሪ አቶ ካሳሁን ዱባሌ እንደገለፁት በትምህርት ዙሪያ የማህበረሰብ የባህሪ ለውጥ ላይ መስራት ችግሮችን ለመቅረፍ ያግዛል በማለት ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።
ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ በትምህርቱ ዘርፍ የሚጠበቁ ውጤቶችን እና ለውጤት የሚያበቁ ዘዴዎችን አስቀምጦ 14 ወረዳዎች ታላማ አድርጎ ወደ ስራ መግባቱን አስተባባሪው ጠቁመዋል።
የቅድመና መደበኛ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ፣ ባሉበት እንዳይደግሙ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ማገዝ፣ በትምህርት የፆታ እኩልነትንና ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንዲሁም የአቅም ማጎልበቻ መስጠት በፕሮግራሙ የተያዘ መሆኑን አቶ ካሳሁን ገልፀዋል።
የመማር ማስተማሪያ ማቴሪያሎች ድጋፍ ማድረግ ፣ተከታታይነት ያለው የሙያ ማሻሻያ መምህራን እንዲያገኙ ማድረግ፣ ከትምህርት ውጪ የሆኑ ተማሪዎች የሚማሩበትን ማመቻቸት፣መረጃዎችን ዲጅታል ማድረግ ለውጤት እንዲያበቁ ከተያዙ ስትራቴጂ ውስጥ ተጠቃሾቹ መሆናቸውን አቶ ካሳሁን ገልፀዋል።
በውይይቱ ከተሳተፉት አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ የትምህርቱን መደበኛ ሥራ የሚያግዝ በመሆኑ በሚገባ በትብብር በመስራት የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አለብን ሲሉ ተናግረዋል ።
በውይይቱ በክልሉ በዩኒሴፍ ከታቀፉ 14 ወረዳዎች፣ከዞን እና ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ተሳትፈዋል ።
