

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውና ”Ethiopia land of origins” በሚል መጠሪያ የተሰየመውን ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን በተያዘው ጥቅምት ወር ከኤርባስ ኩባንያ እንደሚረከብ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ በአፍሪካ የአቪዬሽን መስክ ያለውን የቀዳሚነት ድርሻውን ለማስቀጠል በየጊዜው አዳዲስ አውሮፕላኖችን በማስመጣት እንዲሁም ዓለም አቀፍ መዳረሻዎቹን በማስፋት ላይ ይገኛል።
በዚህም አየር መንገዱ በቅርቡ ከኤር ባስ ኩባንያ የሚረከበው የኤ350-1000 አውሮፕላንም በአይነቱ ልዩና በአፍሪካ የመጀመሪያው ስለመሆኑ አንስተዋል።
አየር መንገዱ ኤ350-900 አውሮፕላኖችን መጠቀም ከጀመረ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ አሁን ላይ ሃያ የኤ350- 900 አውሮፕላኖች በስራ ላይ መሆናቸውን አንስተል።
ኤ350-1000 አውሮፕላን ደግሞ 400 መቀመጫዎች ያሉት እና ለደንበኞች የላቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አየር መንገዱ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2035 በዓመት 67 ሚሊዮን መንገደኞችን በማጓጓዝ 25 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ለማግኘት እየሰራ ነው።
በአሁኑ ወቅትም ባሉት 147 አውሮፕላኖች 139 ዓለም አቀፍና 22 የሀገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።
