




የአህጉሪቱ የመከላከያ ሚኒስትሮች ጉባዔ “አፍሪካ በጠንካራ አንድነት፤ ለሁለንተናዊ ጸጥታና ሰላም!” በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ሲሆን፤ ለቀጣይ ሶስት ቀናት ይቆያል።
በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተጀመረው ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች እና የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በጉባዔው አህጉራዊ የጸጥታ ማዕቀፎችን ማጠናከር እና የሀገራትን ወታደራዊ የትብብር አቅም ማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ምክክር እንደሚደረግ ይጠበቃል።
በዓለም አቀፍ እና በአፍሪካ ደረጃ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ለደኅንነት ስጋቶች ምላሽ መስጠት በሚቻልባቸው ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋልም ተብሏል።
በተጨማሪም አህጉራዊ ወታደራዊ ግብዓቶችንና ትጥቆችን በራስ አቅም ማሟላት በሚያስችሉ ጉዳዮች እና በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሚና ላይ በመምከር ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ይጠበቃል።
ከዚህ ባለፈ አፍሪካ ለሚያጋጥማት ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ምላሽ የመስጠት አቅምን በማሳደግ በወታደራዊ የቴክኖሎጂ ሽግግር የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ እንደሚካሄድ ዘግቧል።
የጉባዔው ተሳታፊ የሆኑት የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ ወታደራዊ አታሼዎች እና ወታደራዊ ተመራማሪዎች የኢትዮጵያን የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የለውጥ እርምጃና የልማት ሥራ እንደሚጎበኙም የኢቢሲ መረጃ ያመለክታል።
