
የኢትዮጵያ ፍላጎት ብሔራዊ ጥቅሞቿን እና ፍላጎቶቿን መሰረት በማድረግ ከሁሉም ጋር ተባብሮ መልማት እና ማደግ መሆኑን ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ገለጹ።
16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ በሩሲያ ካዛን ከተማ ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሚኒስትሮች ልዑካን ቡድን ጋር በመሆን በጉባዔው ላይ ተሳትፈዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ኢትዮጵያ በጉባዔው የነበራትን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ አገራት መሪዎች ጋር ንግድ፣ኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያሉ ትብብሮችን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ብሪክስ ባለው የሕዝብ ብዛት መጠን እና አጠቃላይ ዓመታዊ የምርት መጠን (ጂዲፒ) አኳያ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ያለው ስብሰብ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ ምርቶቿን ወደ ውጭ አገራት በመላክ ገቢዋን ከማሳደግ አንጻር ብሪክስ ትልቅ አቅም መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗና በ16ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ላይ መሳተፏ ትልቅ እድል ይዞ የመጣ ነው ብለዋል።
ብሪክስ አገር ለመገንባት እና ለማሳደግ ለተያዘው ውጥን እንደ አንድ አማራጭ የመጣ ማዕቀፍ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል አገራት ጋር በኢኮኖሚ እና መሰረተ ልማት መስኮች ጠንካራ ትብብር እንዳላት አንስተዋል።
በብሪክስ አማካኝነት ‘ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ” የተሰኘ የፋይናንስ አማራጭ የሚሆን ባንክ እየተቋቋመ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ይህም እድገትን የሚያሳልጡ ስራዎች እና ለመሰረተ ልማቶች ግንባታ ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን እና ፍላጎቶቿን ለማሳካት ከሁሉም ወገን ጋር የምታከናውናቸውን ስራዎች እንዲሁም የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው ሚኒስትሩ ያስገነዘቡት።
የኢትዮጵያ ፍላጎት ከሁሉም ጋር ተባብሮ መልማት እና ማደግ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ልዑክ ከብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ከሩሲያ የንግድ ማህበረሰብ ጋር መወያየቱንና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ማሳየታቸውን አመልክተዋል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ፍሬያማ ተሳትፎ ማድረጓን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
