ኢትዮጵያ የስታትስቲክስ አገልግሎቷን ወደ ዲጂታል ሥርዓት እያሸጋገረች ነው

Spread the love

ኢትዮጵያ የስታትስቲክስ አገልግሎቷን ወደ ዲጂታል ሥርዓት እያሸጋገረች መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሯ ይህን ያሉት በ9ኛው የአፍሪካ ስታትስቲክስ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ ጠንካራ የስታትስቲክስ ሥርዓት እንዲገነባ እየሰራች መሆኗን አንስተዋል።

ለአብነትም በአገር አቀፍ ደረጃ የስታትስቲክስ አገልግሎት ሥርዓቷን ወደ ዲጂታል እያሸጋገረች ነው ብለዋል።

የዚህ ዋነኛ ዓላማም የመረጃ ጥራት ለማረጋገጥ፣መረጃ የማግኘት አቅምን ለማሳደግና በፈጠራ የታገዙ የመረጃ ምንጮችን ለማጠናከር እንደሆነ ጠቁመዋል።

በአገራዊ ስታትስቲክስ ልማት ፕሮግራም የመረጃ ምህዳርን በማስፋት በመረጃ የተመሰረተ ፖሊሲ መቅረፅና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ላይ ያተኮሩ ኢኒሼቲቮችን እየተገበረች ነው ብለዋል።

ዲጂታል የጂኦ-ስፓሻል ሥርዓትና በሞባይል የመረጃ መሰብሰብ ሥርዓትን ለመተግበር ከአገር ውስጥና ከውጭ ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም የመረጃዎችን ወቅታዊነት ብቻ ሳይሆን በውስብስብ ሁኔታዎች ውስጥ ምላሽ የሚሰጥ አገራዊ የስታትስቲክስ ሥርዓትን ለመገንባት እያስቻለን ነው ብለዋል።

የአፍሪካ የልማት ግቦችን ማሳካት ከስታትስቲክስ ሥርዓት መጠናከር ጋር በቀጥታ የተገናኘ መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም የስታትስቲክስ ተቋማት ብቁ ሙያተኞች፣በቂ ፋይናንስና ቴክኖሎጂ እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ የመንግሥታትን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አህጉራዊ፣ቀጣናዊና አገራዊ የስታትስቲክስ ሥርዓትን በማስተሳሰር ጠንካራ የመረጃ አስተዳደር፣ትንተናና አጠቃቀም አቅምን ማጎልበት ወሳኝ እንደሆነም ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

ለዚህም የአፍሪካ ስታትስቲክስ ቻርተርና የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ መምራት መሰረታዊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት፣መልካም አስተዳደርን ለማሻሻልና ሁሉን አቀፍ አህጉራዊ መሻትን ለማረጋገጥ በትክክለኛና የዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት መመራት እንደሚገባ አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ አፍሪካ የ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን የዓለም የስታትስቲክስ አሰራርን በመወሰን ሂደት ጉልህ ሚና እንድትጫወት ማድረግ የሁላችንንም ጥረት ይጠይቃል ነው ያሉት ሲል ኢዜአ ዘግቧል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *