የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ ምግብ ተግባራትን ከገጠር ልማት ኮሪደር ጋር በማስተሳሰር መምራት ይገባል ። ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)

Spread the love

የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ ምግብ ተግባራትን ከገጠር ልማት ኮሪደር ጋር በማስተሳሰር መምራት እንደሚገባ ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ ምግብ መዋቅራዊ አደረጃጀት ለመፍጠር የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተደርጓል።

በምክክር መድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በምግብ ስርዓት እና ስርዓተ ምግብ የተከናወኑ ተግባራት በተሻለ ደረጃ መሻሻሎች የታዩበት መሆኑን ተናግረዋል ።

በክልሉ የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ በማቋቋምና የአማካሪ ካውንስል በማደራጀት ተጨባጭ ለውጦች መኖራቸውን ተናግረዋል ።

ፕሮግራሙ መቀንጨርን መቀነስ፣ሞትን ማስቀረትና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ተልዕኮ ያለው ሲሆን ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር በማስተሳሰር መምራት ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል ።

በክልሉ በተከናወኑ ተግባራት ለውጦች ይኑሩ እንጂ እየተስተዋለ የሚታየው የመረጃ ጥራት ክፍተቶች በትኩረት ሊቀረፉ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ።

በውይይት መድረኩ የብዝሃ ሴክተር የምግብና ስርዓተ ምግብ ፕሮግራም የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም ፣ የፕሮግራሙ መዋቅራዊ አደረጃጀት ለመፍጠር የተዘጋጀ ሰነድና በማስተባበሪያ ጽ/ቤት የተከናወኑ ስራዎች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጓል ።

በፕሮግራሙ የተሳተፉ አካላት በቀረቡት ሰነዶች ዙሪያ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ፕሮግራሙ ሀገር አቀፍ ዓላማ ያለው በመሆኑ በየተቋማቱ ትኩረት በመስጠት መስራት ይገባናል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በቀጣይ ጊዜያት ፕሮግራሙ የራሱ መዋቅራዊ አደረጃጀት ተፈጥሮለት ቀጣይነት ባለው መልኩ ስራዎችን ለማስተባበር እንዲቻል በተጠና አኳኋን መዋቅር መፍጠር ይገባልም ብለዋል።

ተግባራቶችን ባለቤት ሆኖ መምራት እንዲቻል በታችኛው መዋቅር የተዘረጋው የአማካሪ ካውንስል አደረጃጀቶች በተገቢው እውን መደረግ እንደሚገባቸውም አስተያየት ሰጪዎቹ ጨምረው ተናግረዋል።

በተሳታፊዎች በቀረቡ አስተያየቶች በርዕሰ መስተዳድሩ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሁም በቀጣይ የስራ ወቅት መመሪያ በመስጠት ፕሮግራሙ ተጠናቋል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *