ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎትን ማስፋት የሚያስችል ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያ ተደራሽነት ላይ እየተሰራ ነው

Spread the love

ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎትን ማስፋት የሚያስችል ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያ ተደራሽነት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ጤና ሚኒስቴር ለክልሎች፣ ለከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ፣ ለተጠሪ ተቋማትና ለሆስፒታሎች የጤና አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሳልጡ አምቡላንሶችን ጨምሮ 260 ተሽከርካሪዎችን፣ 572 ሞተር ሳይክሎችን፣ 2ሺህ 700 ኮምፒዩተሮችን እንዲሁም የተንቀሳቃሽ ክሊኒክ ድጋፍ አድርጓል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ድጋፉን ለተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት የዜጎችን ጤንነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

ከእነዚህም መካከል የጤና ተቋማትን ተደራሽ የማድረግ፣ የግብዓት አቅርቦትንና በብቁ የሰው ኃይል የማደራጀት ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

ጎን ለጎንም የጤና ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ፈጣን ማድረግ የሚያስችል የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መዘርጋቱንም ገልፀዋል።

ይህም በሽታን ቀድሞ የመከላከልና ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት በመስጠት የዜጎች ጤንነት አጠባበቅ ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የዛሬው የሕክምና ግብዓት ድጋፍም የጤና ተቋማት የዜጎችን ጤንነት ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑንም ተናግረዋል።

የሕክምና አገልግሎትን ለማሳለጥ የሕክምና ግብዓት ብቻ በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *