







በቦንጋ ማዕከል የመሠረታዊ ድርጅት አመራሮችና አባላት “የህልም ጉልበት ለእመርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና በስኬት ተጠናቋል ።
ሰልጣኞቹ ብልፅግና ፓርቲ የተመሠረተበት 5ኛ ዓመት ክብረ በዓል በተለያዩ ሁነቴቶች አክብረዋል።
የክልሉ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው በማጠቃለያ መድረክ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት አመራሩና አባሉ በተሰማራበት መስክ ሁሉ አገልጋይ ተኮር እሳቤን በመላበስ በሁሉም ዘርፍ እመርታ ለማስመዝገብ መትጋት አለበት ብለዋል።
ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባትና ለማጽናት ሠላም ቀዳሚ ጉዳይ በመሆኑ ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም በሚል መርህ ለህዝቡ የሰላምን ትልቅነት በማስገንዘብ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባችሁ ሲሉ ገልጸዋል።
በክልሉ ያሉት እምቅ አቅሞች ና ፀጋዎችን የሀገሪቱን እና የክልሉን ኢኮኖሚ ዕደገት ለመገንባት ምቹ ሁኔታዎች መኖሩን ገልጸው በተለይ ገበያ ተኮር እና ኤክስፖርት የሚደረጉ የቅመማ ቅመም ምርቶች የውጭ የምንዛሬ ድርሻን ለማሳደግ ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
እንደ ሀገር የገጠመንን የኑሮ ውድነት ለመፍታት ቆርጠን መነሳት አለብን ያሉት ኢንጂነር በየነ
ችግሩን ለመፍታት የራሳችንን አቅም አስተባብረንና አቀናጅተን ርብርብ በማድረግ የህዝብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት አለብን ሲሉ ጠቁመዋል።
የክልሉ ፐቭሊክ ሰርቪስና የሠው ሀብት ልማት ቢሮ ም/ኃላፊና የቦንጋ ማዕከል የአስተዳድር ዘርፍ መሠረታዊ ድርጅት ሰብሳቢ አቶ ሳምሶን መለሰ እንደገለጹት ብሔራዊነትን ማዕከል ያደረገ ገዥ ሀገራዊ ትርክት ለመገንባት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን በጽናት ለማስቀጠል አመራሩና አባሉ በትብብር በመስራት ሚናውን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።
አባሉ ከስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በቀጣይ የህዝቡን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉና ሰው ተኮር ተግባራትን ይበልጥ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ስልጠናው ዓለም አቀፋዊ ፣ አህጉራዊ፣ ቀጠናዊና ሀገራዊ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታዎችን ተገንዝቦ ወቅቱን የዋጀና ውጤታማ አመራርና አባል ለመፍጠር ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የገለጹት የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ም/ኃላፊና የቦንጋ ማዕከል የአስተዳደር ዘርፍ መሠረታዊ ድርጅት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር መስፍን ወዳጆ ናቸው።
ከፋፋይ ትርክቶችን እና አስተሳሰቦችን አባሉ በቁርጠኝነት መከላከል በወንድማማችነትና እህትማማችነት ሀገርን የሚያጸናው የብሔራዊነት ትርክት ጎልቶ እንዲወጣ አባሉ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የብልጽግና ህልሞች የተሻለ አፈጻጸም ላይ ለማድረስ የምንችልበት መንገድ ማሰብ አስፈላጊ በመሆኑ ስልጠናው በቂ ስንቅ የተያዘበት እና እርስ በርስ የመገነባበት፣የመተቻቸት የመመካከር ልማድ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።
ፓርቲው ወቅቱን የዋጀ የውይይትና ስልጠና መድረክ እያካሄደ መምጣቱ በአመራሩ እና በአባላት ዘንድ ፣የአስተሳሰብ ና የተግባር አንድነትን ይበልጥ እንዲጎለብት እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ሕዝቦችን ሊያስተሳስሩ የሚችሉ የልማት ፕሮጀክቶችን በትብብር መንፈስ መስራት ያስፈልጋል ያሉት የስልጠና ተሳታፊዎች የሌሎችን ችግሮች በመረዳትና እንደራስ ችግር በመቁጠር በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ችግሮችን መፍታት መቻል አለብን ነው ያሉት።
