የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የአባላቱን አቅም መገንባት ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ

Spread the love

የክልል ተቋማት የቴፒ ማዕከል ፐብሊክ ሰርቫንት የብልፅግና ፓርቲ አባላት በ4ኛ ዙር “የህልም ጉልበት፣ ለእመርታዊ ዕድገት!” በሚል መሪ ቃል ስሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል።

በአባላት ስልጠና ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ መቱ አኩ እንደተናገሩት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ የአባላቱን አቅም መገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል።

እስካሁን የተመዘገበው በሁሉም ዘርፍ የፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አካታች ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ስኬት እንደተጠበቀ ሆኖ አሁንም ቢሆን ከአመራሩና አባላቱ በርካታ ስራዎች አንጻር ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቁ ተናግረዋል።

አቶ መቱ አክለውም ከስልጠናው ያገኘናቸዉን ዋና ዋና ጉዳዮችን ይዘን በተለይ ከሁሉም በላይ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ፈጥረን በጥራት አቅደን በጥራት ለመፈፀም አባሉና አመራሩ የፊት መሪ በመሆን ተጋግዘን ሠላማችንን አጠናክረን ልማታችንን የምናስቀጥልበት ጊዜ ላይ በመሆናችን ሁላችንም በመጠናከር ገዥ ትርክት መገንባት አለብን በማለት በአፅንኦት አንስተዋል።

የቴፒ ብዝሃ ማዕከል የመሠረታዊ ድርጅት አመራሮችም በስልጠናው ወቅት እንደገለጹት ስልጠናው የአመራሩን እውቀት ክህሎትና ልምድ ከማዳበሩ በተጨማሪ ፓርቲውን የሚያጠናክሩ ችግር ፈቺና ለቀጣይ ብልጽግና ጉዞ አጋዥ የሆኑ ገንቢ ሀሳቦችን ለህልም ጉልበት በሁሉ ዘርፍ ለእምርታዊ ዕድገት ግብአት ለማግኘት ያገዘ እንደነበረም ጠቁመዋል።

በፖሊሲ ማዕቀፍ መነሻ በንድፈ ሀሳብና በነባራዊ እውነታዎች ተደግፎ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና በየደረጃው ያለው አመራርና አባላት ዓለም አቀፋዊ ፣ አህጉራዊ፣ ቀጠናዊና ሀገራዊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ሁኔታዎችን ተገንዝቦ ወቅቱን የዋጀና ውጤታማ ተግባር እንዲያከናውንና ሀገሪቱ ያለመችበትን ጉዞ በህልም ጉልበት ወደ ስትራቴጂያዊ ትልም ግብ ለማድረስ ስንቅ እንደሚሆንም ገልፀዋል።

ሰልጣኞቹ አክለውም ስልጠናው ሀገራችን የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ከግብ ለማድረስ አመራሩና አባሉ በአስተሰሰብ ፣ በእውቀት፣ በክህሎትና በሥነ ምግባር ጎልብቶ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃትና በቁርጠኝነት ለመወጣት የሚያስችለውን አቅም ያዳበረበት እንደነበረም ተናግረዋል።

ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ ከባለድርሻ አካላት የተሰጠ ሲሆን በተነሱ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ዙሪያ መግባባት ላይ በመድረስ ስልጠናው ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *