


የተቀናጁ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋትና የምግብ ምርትን ለመጨመር እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ገለጹ።
ከትናንት ጥቅምት 26 እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም እየተካሄደ የሚገኘው “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ዓለም አቀፍ ጉባዔ በዛሬው ዕለትም ቀጥሏል።
በጉባዔው የዛሬ ውሎ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትና የድኅረ-ምርት ብክነት ላይ ያተኮሩ የፓናል ውይይቶች ተካሂደዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ጠንካራ የምግብ ሥርዓት ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሰራች ነው።
በሀገሪቱ ባሉ የተቀናጀ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር የምርት ብክነትን ለመቀነስ፣ የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘምና የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ይህም ለአርሶ አደሮች የገበያ ትስስርና ለበርካቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን አንስተው፤ ይህም የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍና የአጋር አካላት ትብብር ድምር ውጤት ያለውን አስተዋፅዖ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም የግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፉን ማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጉዞ የጋራ ጥረትና ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ እንደሆነ አንስተው፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግልና የመንግሥት አጋርነት ሚና ወሳኝ መሆኑንም ገልፀዋል።
የተቀናጀ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማጠናከር፣ አቅም ግንባታና ለኢንተርፕራይዞች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፉን እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል።
ጎን ለጎንም አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀናጁ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋትና የምግብ ምርትን ለመጨመር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ገርድ ሙለር በበኩላቸው፤ የዓለም ችግር የሆነው ረሃብን ለመቅረፍ ለግብርናው ዘርፍ የሚመደበውን ኢንቨስትመንት ማሳደግና ቴክኖሎጂን ማስፋት አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዘመናዊ የግብርና እና የምግብ አስተዳደር ሥርዓት መገንባት በተለይም በአነስተኛ ማሳ ላይ ለሚሰሩ አርሶ አደሮች የፋይናንስ ተደራሽነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በ2035 ረሃብን ከዓለም ለማጥፋት በየዓመቱ 50 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተናግረው፤ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ይህን እውን ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ገልፀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
