


የጊኒው ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪ ባህ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ጋር በሁለትዮሽና አሕጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
በውይይቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪ ባህ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው አረንጓዴ አሻራ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው በአገራቸው የመተግበር ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ልማት በተለያዩ መስኮች ያላትን ልምድ ወደ ጊኒ ለመውሰድ አስፈላጊው የቴክኒክ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
ሁለቱ አገራት የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች ወደ ተግባር ለማስገባት በትብብር መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ለጊኒ ያላትን ተሞክሮ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ገልፀው፣ አረንጓዴ አሻራ በኢትዮጵያ የውኃ ሃብት ዳግም እንዲያንሰራራ አድርጓል።
የጊኒው ጠቅላይ ሚኒስትር የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የነበሩት ዲያሎ ቴሊ በኢትዮ-ጊኒ ግንኙነት ውስጥ ጉልህ ሚና እንደተጫወቱ መጥቀሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።
