በክልሉ ያለውን እምቅ የግብርና አቅም በተሻለ መልኩ ለመጠቀም የባለድርሻ አካላት ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት ተጠየቀ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ በክልሉ ያለውን እምቅ የግብርና አቅም በተሻለ መልኩ ለመጠቀም የሚስችል የመካከለኛ ዘመን ስትራቴጂካዊ እቅድ ዝግጅት ላይ ለባለድርሻ አካላት በሚዛን አማን ከተማ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታመነ በቀለ በስልጠናው መግቢያ ባደረጉት ንግግር በክልሉ ያለውን እምቅ የግብርና አቅም በተሻለ መልኩ ለመጠቀም በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት ጠይቀዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በክልሉ ያለውን የግብርና ምርት አለኝታ ጥናት ማድረጉን የገለጹት አቶ ታመነ በዚህም በተለዩ የሰብል እና የእንስሳት ሀብት ምርት እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ለመስራት መታቀዱን ገልጸዋል።

በዚህም በተጠናው የክልሉ የግብርና ምርት አለኝታ ሰነድ መነሻ ክልላዊ የአምስት ዓመት የግብርና ዘርፍ ስትራቴጂካዊ እቅድ ለመንደፍ ስልጠናው የባለድርሻ አካላት አቅም የሚገነባ እንደሆነም ተናግረዋል።

የሚዘጋጀው ክልላዊ የስትራቴጂክ የግብርና እቅድ የተሟላ እንደሆነ የግብርና ዘርፍ የባለድርሻ አካላት በስልጠናው እየተሳተፉ እንደሆነ ያብራሩት አቶ ታመነ ሰልጠኝ ባለሙያዎች የስትራቴጂክ እቅድ ክህሎት በማዳበር ከስልጠናው መነሻ በጋራ እቅድ በማዘጋጀት በየደረጃው ባለው መዋቅር ንቅናቄ ተደርጎ ወደ ተግባር ይገባልም ብለዋል።

የሚዘጋጀው ስትራቴጂካዊ የግብርና እቅድ የክልሉን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር አርሶአደሮችን ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነና አጠቃላይ የክልሉን የግብርና ምርት ውጤታማነት የሚያረጋግጥ የጋራ እቅድ መሆኑንም ነው ጨምረው የገለጹት።

ስልጠናው በኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን የባለሙያዎችን ግንዛቤ በማሳደግ በስትራቴጂካዊ እቅድ ዝግጅት ላይ የተሟላ እውቅት እንዲጨብጡ የሚረዳ እንደሆነም ነው የተነገረው።

ለቀጣይ አምስት ቀናት በሚቆየው በዚህም የአቅም ግንባታ ስልጠናና የእቅድ ዝግጅት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች እና ሌሎችም የባለድርሻ ተቋማት የሚመለከታቸው ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *