





የፌዴራል ቱሪዝም ማሰለጠኛ ኢንስቲትዩት ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው በሆቴልና ቱሪዝም ለዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በቦንጋ ከተማ መስጠት ጀምሯል።
የካፋ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ነጻነት ብርሃኑ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የካፋ ዞን ከእናት ቡና መገኛነት ባለፈ የበርካታ መስሂቦች፣ ቅርሶችና ቱባ ባህሎች ባለቤት ናት ብለዋል፡፡
የዞኑ ህዝብ በእንግዳ ተቀይነት፣ በሠላም ወዳድነት፣ በአብሮነት፣ በአንድነትና በመከባበር እንዲሁም በመተሳሰብ ልምድ ያዳበረ በመሆኑ የኅብረ-ብሔራዊ አንደነት ተምሳሌት ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ደነቀ ማሞ የሥልጠናውን መድረክ በከፈቱበት ወቅት የሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥ የዘመነና ለእንግዶ፣ ውብ ምቹና ሳቢ ሊሆኑ ይጋባል ብለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በርካታ ውብና ማራኪ የተፈጥሮ ጸጋዎች ባለበት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደነቀ በለውጡ መንግስት በዘርፉ የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች በመሆናቸው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ሰልጣኞች የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የሆቴል አገልግሎት በመስጠትና ደንበኞችን በትህትና በማስተናገድ የሆቴሎችን ገጽታ ውብ፣ ምቹና ማራኪ ከማድረግ አንጻር በልዩ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባቸው ያሳሰቡት አቶ ደነቀ በቀለም፣ በዘር፣ በሀይማኖት፣ በብሔርና በሌሎች ሳንወሰን ተባብረን ተደጋግፈንና ተጋግዘን ከሰራን ለውጥና ዕድገት እናመጣለን ብለዋል፡፡
የሆቴሎችን አገልገሎት ከማዘመንና የቱሪዝም ዘርፍ ኢኮኖሚውን ከማሳደግ ረገድ እየተደረገ ያለው ተግባር ከመደገፍ አንጻር መንግስት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣም አመላክተዋል፡፡
የፌዴራል ቱሪዝም ማሰለጠኛ ኢንስቲትዩት አቅም ግንባታ ዴስክ ኃላፊ አቶ ተመስገን በቀለ በበኩላቸው ተቋሙ በጥናትና ምርምር፤ በቴክኖሎጂ ሽግግር ፤በማህበረሰብ አቅፍ አገልግሎትና በሌሎችም ዙሪያ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡
ለአንድ ሀገር ለውጥና ዕድገት ትምህርትና ስልጠና ወሳኝ መሆኑን የገለጹት የኢንስቲትዩቱ አቅም ግንባታ ዴስክ ኃላፊ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት ሆኖ በትምህርትና ሥልጠና ውስንነቶች የተጠበቀውን ያህል ጥቅም ሳያገኝ መቆየቱን አመላክተዋል።
ስልጠናው በዘርፉ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለማረም የሚያስችል አቅም የሚፈጥር በመሆኑ ሰልጣኞች ልዩ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
