







የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከጥቅምት 24/2017 ዓ.ም ጀምሮ በሁለት ምዕራፎች ሲያከናውን የነበረውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ዛሬ አጠናቋል።
በሂደቱም በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በአጀንዳ ሀሳቦቻቸው ላይ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተው አጀንዳዎቻቸውን ለይተው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡
ኮሚሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ ባከናወነው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ከክልሉ ሁሉም መዋቅሮች የተመረጡ ከ2 ሺህ 200 በላይ የሕብረተሰብ ክፍል ወኪሎች እና ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ፣ ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው እና ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ የክልሉን አጀንዳዎች ከምክክሩ ባለድርሻ አካላት ዛሬ ከጥቅምት 30/2017 ዓ.ም በይፋ ተረክበዋል፡፡
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ የምክክሩ ማጠቃለያ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከጥቅምት 24/2017 ዓ.ም 30/2017 ዓ.ም ለተከታታይ 7 ቀናት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሁለት ምዕራፎች ሲያከናውን የነበረውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ውጤታማ ሆኖ የተጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል ።
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም የክልሉን አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት አሳታፊ፣ አካታችና ሀሳቦች ያለምንም ተጽእኖ ተንሸራሽረውበታልም ብለዋል፡፡
በክልሉ የምክክርና ሂደት አጀንዳዎችን ከማሰባሰብ ባሸገር ጊዜ ወስዶ ተከባብረውና ተደማምጦ የጋራ አጀንዳዎችን መቅረጽ እንደሚቻል በተግባር የታየበት ነው ያሉት ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ሂሩት ገ/ስላሴ፡፡
በመጨረሻም ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ በክልሉ የተካሄደው ምክክር በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሁሉም የክልሉ አካላት በኮሚሽኑ ስም አመስግነዋል።
የክልሉን የምክክር መድረክ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሙሉጌታ አጎ፣ ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው እና ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገ/ስላሴ በበላይነት ሲያስተባብሩት ቆይተዋል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
