



በክልሉ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ስርጭትን መከላከልና መቆጣጠር ላይ የባለድርሻ ተቋማትና አካላት ሚና እንዲጠናከር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ጠይቋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ለሴክተር መስሪያ ቤቶችና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኤች .አይ.ቪ ሜይንስትሪሚንግ ስልጠና በቦንጋ ከተማ እየሰጠ ይገኛል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ካሰሪ በክልሉ 14 ሺህ የቫይረስ ተጠቂ ይገኛል ተብሎ ግምት ከተሰጠባቸው መካከል እስካሁን ምርመራ ተደርገው 8833 ሰዎች የቫይረስ ተጠቂዎች ተለይተው የጸረ-ኤድስ መድሃኒት እየወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቀጣይ በደማቸው ውስጥ ቫይረስ ያለባቸው ሰዎችን ልየታ እንዲሁም የቫይረስ ስርጭት መጠኑን ለመቀነስ በሚደረገው የመከላከልና መቆጣጠር እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ላይ ሴክተር መስሪያ ቤቶች እና የትምህርት ተቋማት ሚናቸውን በተገባው እንዲወጡ ጠይቀዋል።
አክለውም አቶ መንግስቱ ከሰሪ ቀጣይ ከሴክተር መስሪያ ቤቶችና ተቋማት ጋር የኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠር ግብረሃይል ማቋቋም ፤ድጋፍና እንክብካቤ ፤ ከሰራተኛ የሚቆረጠዉ 0.5 የኤድስ ፈንድ በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ እየዋለ መሆኑን መከታተል ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰሩ አጀንዳዎች መሆናቸውን አንስተዋል ።
በመድረኩ የኤች .አይ.ቪ ኤድስ ወቅታዊ የስርጭት ሁኔታ ፤ብሔራዊ ስትራቴጅክ ፕላን ዓላማ እና ጽንሰ ሀሳብ፤የኤድስ ጥምሪ መከላከል ላይ የተዘጋጀ ሰነድ እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ኤች አይ ቪ ኤድስ ሜይንስትሪሚንግ ተሞክሮ እንደሚቀርብ ከወጣው መረሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።
በፍቅር ከበደ
