



በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የማህፀን በር ካንሰር የመከላከያ ክትባት ዘመቻ በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።
ዘመቻውን በይፋ ያስጀመሩ የክልሉ ጤና ቢሮ ጤናና ጤና ነክ ግብአት ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርና የቢሮው ተወካይ አቶ ሙሉቀን አሰፋ ወላጆችና አሳዳጊዎች እድሜአቸው ከ9 – 14 የሆኑ ልጃገረዶችን በማስከተብ ከማህፀን በር ካንሰር መከላከል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በክልሉ ከ157 ሺ በላይ ልጃገረዶችን ለማስከተብ እቅድ ተይዞ ወደ ተግበራ መገባቱን የገለፁ አቶ ሙሉቀን ክትባቱ ከዛሬ ህዳር 09 ጀምሮ እስከ አርብ ህዳር 13/2017 ድረስ እንደሚቆይ አብራርተዋል።
አቶ ሙሉቀን አሰፋ አክለውም ልጃገረዶች የነገ የሀገር ተረካቢ ስለሆኑ ዛሬ ጤንነታቸው ተጠብቆና በመልካም ስነ ምግባር ማደግ ይገባቸዋል ብለዋል።
የዳውሮ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ አስራት ቸርነት በበኩላቸው በዞኑ ከ42 ሺ በላይ ልጃገረዶችን የማህፀን በር መከላከያ ክትባት ለማስከተብ እቅድ መያዙን አብራርተዋል።
እድሜያቸው ከ9 – 14 አመት ያሉ ልጃገረዶች የመከላከያ ክትባቱን በመውሰድ ራሳቸውን ከማህፀን በር ካንሰር መከላከል ይገባቸዋል ብለዋል።
የፌዴራል ጤና ሚኒስትር የክትባት አማካሪ የሆኑት አቶ ተካልኝ ሙርካ እንደሀገር በትምህርት ቤቶችና በሌሎች የክትባት ጣቢያዎች በዚህ የክትባት ዘመቻ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚጠጉ ልጃገረዶች ክትባቱ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ለክትባቱ ስኬታማነት ወላጆች፣ አሳዳጊዎችና የትምህርት ቤት ማህበረሰቦች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ጥሪ ማቅረባቸውን ደሬቴድ ዋካ ቅርንጫፍ ዘግቧል።
