“የወባ በሽታ የመከላከሉ ተግባር አሁንም በተለየ ትኩረት ህብረተሰባችንን በማሳተፍ መተግበር አለበት” የክልሉ ጤና ቢሮ

Spread the love

በኢትዮጵያ የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ከሚከሰቱ በሽታዎች ወባ በሽታ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ በተለይም ከመስከረም እስከ ታህሳስ ባሉት ወራቶች የወባ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰራጭበት ወቅት ነው።

በሃገራችን ኢትዮጵያ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቀነስ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ሲሆን ከባለፈው አመት ጀምሮ ግን በሽታው በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የመስፋፋት አዝማሚያ እያሳየ መጥቷል፡፡

ከመላ አገሪቱ 75 በመቶ የሚሆኑት አካባቢዎች ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ ሲሆኑ በነዚህ አካባቢዎች ከሚኖሩ ሰዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው፡፡

ከባለፈው አመት ጀምሮ የወባ በሽታ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ የወባ በሽታ ስርጭት በመስፋፋቱ ማህበረሰብ አብዛኛው የበሽታው ተጠቂ ሆኗል፡፡

በሽታውን ለመቆጣጠር ማህበረሰቡ በወባ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ላይ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ፣ የወባ ትንኝ ቁጥጥር ስራዎችን ማጠናከር፣ ህብረተሰቡ አጎበሮችን እንዲጠቀም ማድረግ፣ የወባ በሽታ ምርመራ እና ህክምና አገልግሎት መስጠት ወሳኝ ነው፡፡

ለዚህም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ በክልሉ ለበሽታው ተገላጭ ይሆናሉ ተብሎ የታለዩ አካባቢዎች ላይ የቅድመ መከላከል ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ኢብራሂም ተማም በክልሉ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም አሁንም በርካታ ስራዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረው የወባ ወረርሽኝ ጫና ከፍተኛ በሆኑ ወረዳዎችም ህብረተሰቡን በማሳተፍ ተጨማሪ ስራዎች የሚሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንደ አቶ ኢብራሂም ተማም ገለጻ በክልሉ ባለፉት አራት ወራት በሁሉም አካባቢዎች የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር መከላከልን መሠረት ያደረገ የጤና ፖሊሲን በመጠቀም በርካታ ስራዎች የተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል የተዘረጋው የአሰራር ስርዓት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት የቢሮው ኃላፊው አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ካለው የበሽታው ስርጭት ጫና አኳያ የመከላከሉ ተግባር በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ ጤና ባለሙያዎቻችን፣ የጤና ኤክ/ን ሰራተኞቻችን እና የሴቶችና ወጣት አደረጃጀቶቻችን አሁንም በተለየ ትኩረት በመቀናጀት ወደ ተግባር በመግባት የበሽታውን ጫና መቀነስ እንዳለበት ተናግረዋል።

ባለፉት አራት ወራት በቅንጅት የተሰሩ ስራዎች ላይ በጉድለት የተለዩት አፈጻጸሞች ላይ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ገልጸው ይህንን ለማጠናከር በወረዳና በቀበሌ ደረጃ ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ የክልል ጤና ቢሮ አመራርና ባለሙያ ስምሪት በቢሮ አመራሮቻችንና ዳይሬክቶሬቶች የሚመራ የባለሙያ ቡድን በሁሉም ዞን ለሁለት ወራት በላይ በስምሪት ስምሪት መሰጠቱን አቶ ኢብራሂም ገልጸዋል። በተመሳሳይ ለሠራተኛ ዙር የክልሉ የድጋፍ ቡድን ቀበሌን መሰረት ያደረገ የወባ በሽታ ቁጥጥር ተግባርና መደበኛ ሥራ ለማጠናከር ያለመ ስምሪት ተቀብለው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡

የወባ መከላከልና መቆጣጠር ቅንጅታዊ አሰራርን በተመለከተ ከክልል እና በተዋረድ ከሚገኙ ምክር ቤቶች ጋር የግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በመስራት ድጋፍ ፣ክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት በሁሉም ዞኖች የወባ መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት የመስክ ምልከታ መደረጉንና ከከፍተኛ እና መካከለኛ የትምህርት ተቋማት፣ከክልል ትምህርት ቢሮ፣ ከክልል ግብርና ቢሮ ጋር በቅንጅት በታችኛው መዋቅር እየተሰራ የሚገኝ መሆኑን አቶ ኢብራሂም ተማም የገለፁት ።

በወባ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ በጤና ተቋማት ዘወትር ከሚስጠው የጤና ትምህርት በተጨማሪ የወባ መልዕክቶችን ተደራሸ ለማድረግና በክልሉ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ቋንቋዎች መልዕክት ማስተላፍ እንዲቻል በክልሉ ባሉ ሚዲያዎች በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በቦንጋና ሚዛን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ፣በሚዛን ፋና ፣በካፋ ቲቪ፣በዋካ ኤፍ ኤም ፣በቦንጋ ማሀበረሰብ ሬዲዮ እና በማሻ ኤፍ ኤም ጣቢዎች ትምህርት ሰጪ የወባ መልዕክቶች እንዲተላለፉ ለአራተኛ ዙር ውል ተገብቶ በአሁኑ ሰዓት መልዕክቱ እየተላለፈ እንደሚገኝ የቢሮው ኃላፊ አስታውቀዋል ።
በክልሉ በቀበሌ ደረጃ በተደረገው ድጋፍዊ ክትትል የወባ ትንኝ ቁጥጥር ተግባራት አኳያ የአልጋ አጎበር ስርጭትና አጠቃቀም ክትትል በተደረገ ንቅናቄ ሳይሰራጭ የከረመ 76 ሺህ 420 አጎበር ማሰራጭት የተቻለ እና አራት ወር ውስጥ 607 ሺህ 063 ቤቶች ተጎብኝተው 218 ሺህ 007 ከአጠቃላይ 36% አባወራ/እማወራ በአግባቡ ሰቅለው የማይጠቀሙ በመሆናቸው ግንዛቤ ማስጨበጥና የአጎበር አሰቃቀል ትምህርት ተሰጥቷልም ብለዋል።

የቤት ለቤት ኬሚካል ርጭት ከወባ መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት አንዱና ከፍተኛ ወጪ ከሚጠይቁ ስትራቴጅዎች አንዱ ሲሆን ባለፉት አራት ወራት በስምንት ወረዳዎች ውስጥ ካሉ በተመረጡ 166 ቀበሌዎች መካከል በ66 ቀበሌዎች በሃምሌና ነሐሴ ወር ላይ የቤት ለቤት ኬሚካል ርጭት ማካሄድ ተችሏል።
81,370 ዩኒት ስትራክቸር ከሚጠበቀው ውስጥ 85,511 ዩኒት ስትራክቸር መርጨት የተቻለ ሲሆን አፈጻጸሙም 99.93 % ማድረስ ተችሏል።
የትንኝ እጭ መግደያ ኬሚካል አጠቃቀም
በክልሉ ቀደም ብሎ በተለዩ ጊዚያዊና ቋሚ የወባ መራቢያ ቦታ ላለባቸው ወረዳዎችና ከተማ አሰተዳደሮች 254,526ሚሊ ሊትር የወባ ትንኝ ዕጪ መግደያ ኬሚካል ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ከበሽታው ስርጭት እና ጫና አንጻር ሁለቱም አይነት የኬሚካል ዓይነቶች ዕጥረት መኖሩንና ይህንንም ለጤና ሚኒስቴር በማሳወቅ ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑን ገልፀዋል።
የአካባቢ ቁጥጥር ስራዎች በሚመለከትየወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ማፋሰስና መዳፈን በተመለከተ 1,177,654.9 ካ.ሜ ቋሚ እና ጊዚያዊ የወባ መራቢያዎች የተለዩ ሲሆን በህብረተሰባችን ጠንካራ ተሳትፎ የማፋስስና ማዳፈን ስራ ተሰርቷል።
የበሸታ ቅኝትና አሰሳ በሁሉም ቀበሌዎች ዕለታዊ የበሸታ ቅኝትና አሰሳ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን የህክምና አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሸ ለማድረግ ከዚህ በፊት የወባ ምርመራና ህክምና በማይሰጡ ጤና ኬላዎች የወባ ምርመራና ህክምና እየተሰጠ እንደሚገኝ አቶ ኢብራሂም ገልፀዋል ።

በክልሉ ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በተፈጠረው የወባ ምርመራና ህክምና ንቅናቄ 530 ሺህ 369 ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸው 339 ሺህ 877 ሰዎች ላይ ወባ በሽታ የተገኘባቸው ሲሆን የመገኘት ምጣኔ 64 % ሆኗል።

በዚህ አራት ወር ውስጥ 519 ሺህ 825 ሰዎችን መመርመር የሚያስችል ፈጣን የወባ መመርመሪያ ኪት፣ ለ677 ሺህ 260 ተመላላሸ ታካሚዎችን ማከም የሚያስችል ኳርተም እና ክሎሮኪን እንዲሁም ለ4 ሺህ 626 ተኝተው ለሚታከሙ ሰዎች የሚሆን በመርፌ የሚሰጥ የወባ መድኃኒት እና ግብዓት አቅርቦት እስከ ጤና ኬላዎች ድረስ ማድረስ ተችሏል ነው ያሉት።

ከህገ ወጥ መድኃኒት ቁጥጥር አንጻር የተከናወኑ ተግባራት በክልሉ ሁሉም ዞኖች ከክልሉ የፖሊስ አካላት ጋር በመተባበር የተጠናከር ክትትልና ማህበረሰቡ ጥቆማ ማቅረብ የሚቻልበት ሥርዓት በመዘርጋቱ በህገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ መድኃኒቶችን ለመግታት የክልላችን ግ/ጥ/ቁ/ ባለስልጣን እና 1ኢትዮጲያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመተባበር በሁሉም ዞኖች ቁጥጥር በማካሄድና በህዝብ ጥቆማ ያልተመዘገበና ያልተፈቀደ መድኃኒት ተይዞ በህግ የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው።

በቀጣይም በወባ መከላከልና መቆጣጠር ተግባራት በተጠያቂነት አሰራር ስርዓት እየተሰራ በመሆኑ ከምን ጊዜውም በላይ ሙያዊ ዲስፒሊን በመጠበቅ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።

እንደ ክልል የወባ ጫና ከሁለት ወር በፊት ከነበርንበት ሲታይ የተወሰነ መሻሻሎች ቢኖሩጭ የክረምት ማታን ተከትሎ የወባ ጫና ሊጭምር ስለሚችል የመከላከልና መቆጠጣጠር ተግባሩን የበለጠ በቅንቾት ማጠናከር የሚያስፈልግ መሆኑን ተናግረዋል ።

ወባን ከመከላከልና መቆጣጠር አንጻር የሚስተዋሉ የአልጋ አጎበር በአግባቡና ሁል ጊዜ ያለመጠቀም፣ የአልጋ አጎበር ላልተፈለገ ዓላማ የመጠቀም ዝንባሌ፣ ለግለሰብ የታዘዘን መድኃኒት ለሌላ ማጋራት እና ህብረተሰቡ በጤና ባለሙያዎች እና በጤና ተቋማት የሚተላለፉ መልዕክቶችን በአግባቡ አለመተግበር ውስንነቶችን መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡

እነዚህን ጉድለቶችን በማረም እና የህመም ስሜት ያላቸው ሰዎች ወደ መንግስት ጤና ተቋም እንዲሄዱ በማድረግና ህክምናቸውን በአግባቡ እንዲካታተሉ ከማድረግ አኳያ የተጀመሩ ተግባራት ሳይቆራረጡ እንዲቀጥሉ የማድረግ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለወባ እና ለሌሎችም የጤና አገልግሎት ስራዎች ለጤና ተቋማት የሚላኩ ግብዓቶች በአግባቡ ስራ ላይ እንዲውል መደረግ እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን በተለይ ህገ-ወጥ የመዲሀኒት ቁጥጥር ስራ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጋራ በቅንጅት መሰራት እንደለበት አቶ ኢብራሂም አመልክተዋል።

ለወባ በሽታ ህክምና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የህዝብ ንቅናቄ በማጠናከር መሰረታዊ የመከላከል ዘዴዎች ላይ ህ/ሰቡ በትኩረት እንዲሰራ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ከጤና ኬላዎች ጀምሮ ባለው የጤና ተቋማት የወባ በሽታ ምርመራ እና ህክምና አገልግሎት በተጠናከረ ሁኔታ መሰጠት እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን የግብዓት እጥረት በጤና ኬላዎች እንዳይፈጠር ጥብቅ ድጋፍ እና ክትትል የሚደረግ መሆኑን አብራርተዋል።

ወቅቱ ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ለወረርሽኙ መስፋፋት ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር በመሆኑ ለዚህም ሀሉም ባለድርሻ አካላት በሽታውን ከመከላከልና ከመቆጣጠር ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለበቸውም አቶ ኢብራሂም አሳስበዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *