




ኢትዮጵያ አህጉራዊ ግቦችን የሚያሳኩ ዘላቂና አካታች መሠረተ ልማቶችን እየገነባች መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ።
ስምንተኛው የአፍሪካ መሠረተ-ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ሳምንት በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)፤ ዛሬ የምንገነባው መሠረተ ልማት የነገ አህጉራዊ እጣ ፈንታን የሚወስን ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ወሳኝ አህጉራዊ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት በቂ የፋይናንስ አቅም አስፈላጊ በመሆኑ ዘላቂ የመሠረተ ልማት ፋይናንስ አማራጭን ማፈላለግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
በአፍሪካ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ የኤሌክትሪክና የንፁህ መጠጥ ውሃ አገልግሎትና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን እያገኘ አይደለም ሲሉም ነው የተናገሩት።
የአፍሪካ መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም በአፍሪካ የመሠረተ ልማት ትስስርን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ስርዓት ለመገንባት እየሠራች መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካን ሽግግርና ብልፅግና የሚያሳኩ በአየር፣ በየብስና በባህር የትራንስፖርት ስርዓት አህጉራዊ ትስስርን ማጠናከር የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶችን እየገነባች መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዘላቂና አካታች መሠረተ ልማት ግንባታ የሰጠችው ትኩረት ቀጣናዊ የመሪነት ሚናዋን የሚያሳይ መሆኑን አንስተው በቀጣይም ለአህጉራዊ ትስስር ሚና ያላቸው ሜጋ ፕሮጀክቶችን መገንባቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
