



በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በካፋ ዞን በቦንጋ ከተማ እየተገነባ ያለው የመናኸሪያ ግንባታ ነሐሴ 21 ቀን 20/14 በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ መሠረተ ድንጋይ ተቀምጦለት ወደ ስራ መገባቱ ይታወቃል፡፡
ይህ ከክልሉ መንግስት በተመደበ በ94 ነጥብ 1ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ በጆስ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ በተወሰነ የግል ድርጅት እየተገነባ ያለው ዘመናዊ መናኸሪያ ሲሆን ከ11 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ በሆነ መሬት ላይ ያረፈ መሆኑን የግንባታ ድርጅቱ አስተባባሪ አቶ ፊልሞን ሰለሞን ገልፀዋል።
የመናኸርያ ግንባታ ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመንገደኞች ማረፊያ ፣ ለተሳፋሪዎች የትራንስፖርት ቲኬት መስጫ ክፍሎች፣ መሰብሰቢ አዳራሽ ፣መጸዳጃ ቤት፣ የመዝናኛ ካፌና ሌሎችም አገልግሎቶች ፣ የአንድ አገልግሎት መስጫ አስተዳደር ቢሮዎች እና ሌሎች አገልግሎቶቹን ያካተተ መሆኑንም አቶ ፊልሞን አንስተዋል፡፡
ግንባታውም በፍጥነት ተጠናቆ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት እንዲሆን ድርጅቱ ከኮንስትራክሽን ባለስልጣን፣ ከመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ፣ ከክልሉ ፋይናንስና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካለት ጋር በመነጋገር ችግሮቹን በመፍታት በአሁኑ ላይ ስራው በተሻለ ፍጥነትና እየተከናወነ መሆኑን አብራርቷል፡፡
በመናኸሪያው የተለዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ 3 ህንፃዎች እንዳሉት የጠቆሙት አቶ ፊልሞን ግንባታው የህንፃዎቹ ከ98 ከመቶ በላይ መጠናቀቁን ተናግረዋል።
የግባታው ቀሪው ስራው አሁን የመናኸሪያው ግንባታ በአብዛኛው የሜዳ ማስተካከል መሆኑን አንስቶ ለዚህም የመጀመሪያ ዙር የመሬት ቆራጣ መከናወኑን እና ሁለተኛ ዙር ለመጀመር የቦታው አቀማመጥ ብዙ ለግንባታ ስራው ምቹ ባለመሆኑ ተጨማሪ መሬት የሚፈልገው በመሆኑ የወሰን የማስከበርና ካርታ እንዲዘጋጅ በማድረግ ስራውን ለማጠናቀቅ በጉዳዩ ከስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡
የሚያስፈልገውን ማሽነሪዎች አስገብተው ሜዳ የማስተካከልና ሌሎች ተያያዥነት ያለቸውን ስራዎች በመስራት የመናኸሪያ ግንባታውን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ እንደሚያስረክቡም የግንባታ ተቋራጩ አስተባባሪ አቶ ፊልሞን ሰለሞን ጠቁመዋል።
ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲያስችል ክልሉ ፣ዞንና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ለስራው ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
በተከተል ወ/ሚካኤል
