በክልሉ ከ8 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ ነው

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 8 ሺህ 4መቶ 19 ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

እየተሰጠ የሚገኘው የተማሪዎች ምገባ አገልግሎት ልዩ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንደሆነም ተገልጿል።

የቢሮ ምክትል ኃላፊና የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ደስታ ገነመ እንዳሉት፥በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ከሚተገበሩ ኢኒሼቲቮች መካከል የተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መረሐ ግብር አንዱ ነው፡፡

የምገባ መርሐግብሩ የተማሪዎች መጠነ መቅረትና ማቋረጥ ከመቀነስ ባሻገር የተማሪዎች ትምህርት ቤት ተሳትፎ በማሻሻል በመማር ማስተማር ሂደት ትምህርታቸውን በንቃት በመከታተል ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚያግዝም ጠቅሰዋል።

በክልሉ የተማሪዎች ምገባ መረሐ ግብር በ2017 ትምህርት ዘመን በመጀመር ገና በጅምር ላይ የሚገኝ ሲሆን እስካሁን ባለው ሂደት በ48 ትምህርት ቤቶች ምገባ አገልግሎቱ እየተሰጠ እንደሆነም የቢሮ ምክትል ኃላፊው አስረድተዋል።

የራስ አገዝ ምገባ ባለቤት ማህበረሰቡ ነው።መሠረታዊ ሀሳቡ 5 ኪ.ግ እህል ለተማሪ በሚል ኢንሸትቭ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ከማህበረሰብ፣ ከትምህርት ቤቶች ከሚገኘው ምርት፤ ከባለሀብቶች፣ ረጂ ድርጅቶችና ግለሰቦች በሚሰበሰብ ሀብት የሚከናወን በመሆኑ የራስ አገዝ የምገባ ሂደትን የሚከተል ነው።

የምገባ መረሐ ግብር ባልተጀመረባቸው የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች ማህበረሰቡን በማወያየት፣የተማሪ ወላጆችን በማሳተፍ እንዲጀምር ይደረጋል ብለዋል።

የተጀመረው በተገቢው እንዲቀጥል፣መረሐግብሩ ባልተጀመሩባቸው ትምህርት ቤቶች እንዲጀምር በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እስከ ትምህርት ቤት፣ የቀበሌ አስተዳዳሪዎችና የመምህራኞች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ እነዚህ አካላት ተግባሩ የትውልድ ግንባታ ጉዳይ ስለሆነ ለኘሮግራሙ ቀጣይነትና መስፋፋት ሚናቸውን እንዲወጡም ኃላፊው ጠይቀዋል ።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *