ሴቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች ሁሉ ዓቀፍ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በቁርጠኝነትና በቅንጅት እየተሰራ ነው :-የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶችንና ወጣቶችን ተሳትፎ እና ተጠቀሚነት ማረጋገጥ፣ የህፃናትን መብትና ደህንነት እንዲከበር ማድረግ፤ በማህበራዊ ዘርፍም የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ደህንነት፣ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ የቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ ገልጸዋል።

ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ የአመራር ፑሉን የማጠናከር ስራ አስፈላጊ በመሆኑ ለአመራርነት እና ለውሳኔ ሰጪነት ብቁ የሆኑ ሴቶችን በማሰልጠን የመመልመል ስራ የተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ገነት ከ9ሺ7መቶ በላይ ሴቶች የአመራርነት ስልጠና የወሰዱ መሆናቸውንና ከዚህ ውስጥ የተመለመሉት 57 ሴቶችን በየደረጃው ወደ አመራርነት የማምጣት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

ሴቶች በኢኮኖሚ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትልቅ ስራ እየተሰራ እንዳለ እና ከዚህም አንዱ ሴቶች በቁጠባ ላይ ተሳትፈው የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሻሽሉ ማድረግ ነው ያሉት ኃላፊዋ በክልሉ 44 ሺህ 4 መቶ 73 የሚሆኑ በሴቶች ቁጠባ እንዲሳተፉ መደረጉንና 78 ሚልዮን 913 ሺህ ብር በላይ መቆጠብ የተቻለ መሆኑን ገልፀው ከዚህም 21 ሺህ ከ170 በላይ የሚሆኑ ሴቶች 43 ሚልዮን 667 ብር በላይ የሆነ ብድር ተጠቃሚ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ሴቶች በኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሴቶች ልማት ህብረት ላይ ያለውን ቁጠባ ወደ አንድ በማምጣት የሴቶች ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር እንዲደረጂ መደረጉንና 9 ሺህ 632 ሴቶች በሴቶች ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበር ስር እንዲታቀፉ መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ሴቶች ድርብ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ የጊዜ እና የጉልበት ቆጣቢ በሆኑ ቴክኖሎጂዎች ጋር እራሳቸውን እንዲተዋወቁ እና ተጠቃሚ እንድሆኑ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ወ/ሮ ገነት ጠቁመዋል፡፡

29ሺህ 960 ሴቶች የጊዜ እና የጉልበት ቆጣቢ በሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ የማድረግ ስራ ተሰርቷል ብለዋል ኃላፊዋ፡፡

ሴቶች የመደራጀት መብታቸውን ተጠቅመው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡

በቀድሞ የሴቶች ልማት ቡድን አባል የሚያደርጋት ሴት ዕድሜን እና ከዚህ በፊት የነበረውን የ1ለ5 አደረጃጀትን በመቀየር የሴቶች ልማት ህብረት ስያሜ በመቀየር ከስር ያለውንም ወደ 1ለ 10 ትስስር በመቀየር አደረጃጃትና አሠራር መመሪያ በማዘጋጀት የመጠናከር ስራ መሰራቱን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

በአሁኑም 11 ሺህ 388 የሴቶች ልማት ህብረት አደረጃጀቶችን ማጠንከር ተችሏል ያሉት የቢሮው ኃላፊዋ ወ/ሮ ገነት የሴቶችን ሁሉ አቀፍ ተሳታፊና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተቋማት የሴት አደረጃጀቶችን ማዕከል አድርገው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የህፃናትን መብት ለማክበርና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ የወሳኝ ኩነት ዘርፍ ጋር በመቀናጀት የህፃናት የልደት ምዝገባ መሰጠት እንዳለበት ለወላጆች ግንዛቤ በመፍጠር፤ ክትትልና የልደት ሰርተፍኬት ተደራሽነትን የማረጋገጥ ስራ ተሰርቶ 35 ሺህ 393 ህፃናት የልደት ሰርተፍኬት እንዲያገኙም መደረጉን ጠቁመዋል።

በህፃናት ላይ የሚደርሰውን ያለ እድሜ ጋብቻ ለመከላከል ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት በተሰራው ስራ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው በትምህርት ቤቶች ውስጥም የህፃናት ጥቃትና መድሎ ነፃ የሆነ ትምህርት ቤቶችንም መፍራት ተችሏል ብለዋል።

ህፀናት በህፃናት ፓርላማ እንዲደራጁ በማድረግ ንቁ ተሳታፊና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን እንዲላማዱ ከቀበሌ እስከ ክልል ባሉት ምክር ቤቶች በሚደረጉ ጉባኤዎች ተገኝተው ሂደቱን እንዲከታተሉ አሰራሩን የመየትና በቀጣይም የራሳቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት ወ/ሮ ገነት፡፡

የወጣቶች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከታች ጀምሮ በማህበር፣ በፌዴሬሽን እና መንግስታዊ ባልሆኑ አደረጃጀቶች ተደራጅተው መብትና ደህንነታቸውን እያስጠበቁ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

ወጣቶች በክረምት እና በበጋ ወራት በጎ ፍቃድ አገልግሎት 644 ሺህ 558 ወጣቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን የበጎፈቃደኝነት አገልግሎት ተግባር በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል ወደ ማድረግ ስርዓት እየመጣ መሆኑን ወ/ሮ ገነት መኩሪያ አንስተዋል፡፡

በዚሁ በክረምት እና በበጋ ወራት በጎ ፍቃድ አገልግሎት1ሚሊየን 102 ሺህ 202 የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ሆኗል ብለዋል፡፡
በአገልግሎቱ 604 ሚሊየን 422 ሺህ 460 ብር በላይ ከመንግሥት እና ከማህበረሰብ ይወጣ የነበረውን ወጪ ማዳን መቻሉን ወ/ሮ ገነት መኩሪያ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ አካል ጉዳተኞች በታለየ መልኩ በሁሉም አደረጃጀቶች ልዩ ትኩረት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንና አካል ጉዳተኞች የህክምና እና ድጋፍ እንዲያገኙ የአካል ጉዳተኞች የህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ተገንብተው ባለመጠናቀቁ ከአርባምንጭ ተሃድሶ ማዕከል ጋር በመተባበር በቀጠሮ እየተመላለሱ የህክምና አገልግሎት ድጋፍ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሴቶች፣ ህፃናትና፣ ወጣቶችና የአረጋዊያን እና አካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በየደረጃው ያለው ባለድርሻ አካላት በጋራ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው የገለጹት ወ/ሮ ገነት መኩሪያ ከፍተኛውን የህብረተሰብ ክፍል አካላት ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ካልተረጋገጠ ልማት ማምጣት የማይቻል መሆኑን አሳስበዋል፡፡

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *