የአቶ ተዘራ ወ/ማሪያም አጭር የሕይወት ታሪክ

Spread the love

አቶ ተዘራ ወ/ማሪያም ሱራ ከአባታቸው ከሃምሳ አለቃ ወ/ማሪያም ሱራ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ በላይነሽ ጮቤ በቀድሞው ከፋ ክፍለሀገር በኤላ አውራጃ በአመያ ከተማ በ1973 ዓ/ም ተወለዱ።

ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የአንደኛ ደረጃ ትምርህታቸውን በአከባቢያቸው ተከታትለው የኮሌጁ ትምርህታቸውን በአርባምንጭ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በመምህርነት ተመርቀው በኦሽካ ዴንቻ ፣በኮንታ ኮይሻ፣በጨበራ ሻሾ ፣በኮዳ ማጂ፣በገንጂ ገነት፣በመዳየጃ በማስተማር ሙያና በጪዳ ሙሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በርዕሰ መምህርነት በቅንነትና በታማኝነት አገልግለዋል ።

ከዚያም ለትምህርት ባላቸዉ ልዩ ፍላጎት የመጀመሪያ ዲግሪያቸወን በትምህርት አመራርነት ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ፣የሁለተኛ ዲግሪዉን ቢዝነስ አስተዳደር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል።

አቶ ተዘራ ባላቸው መልካም የስራ አፈጻጸም እና በህዝብ ዘንድ ካላቸው ተቀባይነት በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነትና የአሁኑ ኮንታ ዞን ልዩ ወረዳ በነበረ ጊዜ የልዩ ወረዳወ ዋና አስተዳዳሪ በመሆን፣ በቀድሞው የደቡብ ክልል የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ በመሆንም አገልግለዋል ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሲደራጅ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በትጋት በመስራት ክልሉ በሠላማዊ መንገድ እንዲደራጅ ትልቅ ሚና ተጫውቶ ነበረ።

አቶ ተዘራ የተጣለበትን የህዝብና የመንግሥትን ሀላፊነት በፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆን እና በክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ በመሆን ለህዝብ ጥቅም የሰሩ ሲሆን ከመንግሥት ሀላፊነት ባሻገር በማህበራዊ ጉዳዮች ጠንካራ ተሳትፎ የነበራቸው ህዝብን በኃላፊነት ባገለገሉባቸው ተቋማት ሁሉ ተግባቢ ሰርቶ የሚያሰራ ትጉህ አገልጋይ በመሆናቸው ከተለያዩ ተቋማት የእውቅና ሽልማት ያገኙ መሪ ነበሩ።

አቶ ተዘራ በግል ባህሪያቸው ለተቸገረ ደራሽ ፣ መካሪ፣ ተግባቢና ተጫዋች የተጣለበትን ሀላፊነት በተግባር ለመወጣት ቀን ከለት የሚለፋ የተግባር ሰው ጠንካራ መሪ ሲሆን ዓ/ም በሥራ ገበታ ላይ እያሉ በገጠማቸው ድንገተኛ የጤና እክል ምክንያት በጅማ ሪፈራል ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው በቀን 20/7/2016 ከዚህ ዓለም በሞተ ተለይተዋል።

አቶ ተዘራ ወ/ማርያም ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ነበሩ።

ከጎናችን በድንገት ያጣነውነውን የወንድማችን የአቶ ተዘራ ወ/ማርያም ነፍስ ይማር።

ለወዳጅ ለዘመድና ለስራ ባልደረቦቹና ለክልላችን ህዝብ መጽናናትን ፈጣሪ ይስጥ።

መጋቢት 22/2016

አመያ ኮንታ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *