


በግብርናው ዘርፍ የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች የዘርፉ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እያስቻሉ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱ በግብርናው እሴት ሰንሰለት ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በጥናትና ምርምር መለየት፣ ለማነቆዎቹ የመፍትሔ ሃሳብ ማመንጨት ላይ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዘርፉ የመፍትሔ ሃሳብ ማመንጨት ብቻ ሳይሆን የመፍትሔ ሃሳቦች ገቢራዊ እንዲሆኑ በማስቻል ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ተደራጅተው በሜካናይዜዥን እንዲያመርቱ፣ ግብዓት በቀላሉ እንዲያገኙና የተመረተውን ምርት በጋራ ሰብስበው መሸጥ እንዲችሉ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ኢንስቲትዩቱ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት በግብርናው ዘርፍ የሀገሪቱ የልማት አቅጣጫን ለመቀየሰ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስታውቀዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ገለጻ ኢንስቲትዩቱ ምርታማነት እንዲያድግ አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ የግብርና ኬሚካል እንዲያገኙ እንዲሁም ስልጠና ማግኘት የሚችሉበት የአንድ መስኮት አገልግሎት እየተስፋፉ ይገኛል።
እንዲሁም ትራክተር፣ኮምባይነር፣ የጭነት ተሽከርካሪዎች፣መጋዘኖች ፣ የዘር ማበጠሪያና ማሸጊያ ማሽኖች ለኅብረት ስራ ማህበራት በማቅረብ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።
በተከናወኑ ተግባራት የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እየጨመሩ መምጣቱን አንስተው፥ በተለይ በኩታ ገጠም ተደራጅተው የሚያርሱ አርሶ አደሮች 30 ከመቶ የምርት ጭማሪ ማሳየታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የአርሶ አደሮቹ የገቢ መጠን ማደግ መቻሉን አመልክተዋል።
በቀጣይ በኩታ ገጠም የሚታረሱ አካባቢዎች ላይ የምርት ማከማቻ መጋዘኖች መገንባት፣ የተመረተው ምርት ላይ እሴት መጨመርና ለውጥ ያመጡ አርሶ አደሮችን ወደ ኢንቨስትመንት ኩባንያ ማሳደግ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምር የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ለሁሉም ክልሎች መዘጋጀቱንም አመላክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
