



“ትውልድ በመምህር ይቀረፃል ፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ ቃል የካፋ ዞን መምህራን ውይይት ማጠቃለያ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ትምህርት የልማት ሁሉ መሠረት መሆኑን ጠቁመው ፤ ይህም በትውልድ ቅብብሎሽ የሚቀጥልና ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚን የሚገነባ ነው ብለዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ማፍራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
አስተማማኝ የሆነ ኢኮኖሚ ከመገንባት አኳያም የትምህርት ፋይዳ ጉልህ መሆኑን ጠቁመው ፤ ተገቢና ትክክለኛ የሆነ ማህበራዊ አገልግሎትን መስጠት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ የአንድ ሀገር ልማትና ብልጽግና የሚረጋገጠው በትምህርት በመሆኑ ፤ በዘርፉ አስፈላጊውን አስተዋጽኦ በማበርከት ኃላፊነት የሚሰማው ትውልድ ማፍራት ይገባል ብለዋል፡፡
በዘርፉ ያጋጠሙ ስብራቶችን ለመጠገን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል ያሉት አቶ እንዳሻው ፤ የትምህርት ምዘና ሥርዓቱን የማሻሻል ሥራ መከናወን መቻሉንም አንስተዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች ቁሳቁሶችን የማሟላትና በቴክኖሎጂ የመደገፍ ተግባር መከናወኑን አክለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በትምህርት ለትውልድ እንቅስቃሴ በርካታ ትምህርት ቤቶችን መገንባት ስለመቻሉ ነው የገለጹት፡፡
ቀጣይነት ያለው ሥራ በትምህርት ቤቶች ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው ፤ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎችና ለመምህራን ምቹ መሆን እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ቤት አምባሳደሮች በየደረጃው ውይይት በማድረግ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ የተጀመረው ጥረት አበረታች መሆኑንም አክለዋል፡፡
የሚስተዋለውን የትምህርት ብክነት ለመቀነስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት ማጣት አሳሳቢ መሆኑን የገለጹት አስተዳዳሪው ፤ በተለይ ምንም ተማሪ ባላሳለፉ ትምህርት ቤቶች ላይ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን በመጠቆም በ2017 የትምህርት ዘመን የተሻለ ውጤት ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡
የካፋ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ መሸሻ በበኩላቸው ፤ ትምህርት የአንድ ሀገር የብልጽግና መሠረት መሆኑን አንስተው ፤ የትሞህርት ዘርፉ ላይ ሪፎርም ተደርጓል ብለዋል፡፡
ዘርፉን የበለጠ ውጤታማ ለማደረግ በየደረጃው ያሉ መምህራን ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ለውይይት የተዘጋጀውን ሀገራዊ ሰነድ የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ አቅርበዋል ሲል ቦንጋ ኤፍኤም ዘግቧል፡፡
