ሪፖርታዥ

Spread the love

“አረንጓዴ አሻራን ከቡና ልማት ጋር በማስተሳሰር እየተሠራ ነው፡-

አቶ አሥራት መኩሪያ የደቡብ ምዕራብ ኢትዩጵያ ሕዝቦች ክልል ቡና፣ ሻይና ቅማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ እንደ ሀገር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተግባራዊ በማድረግ ምድርን አረንጓዴ የማልበስ ስራ ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ ለቡና ልማትና ምርት ዕድገት ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል ብለዋል፡፡
በክልላችን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፌ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸዉ ችግኞች በተለይም እንደ ቡና ያሉ ችግኞች ተከላ ላይ ትኩረት በማድረግ እየተተገበረ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ አስራት በክልላችን እየለሙ ካሉ የግብርና ልማት ሥራዎች ውስጥ ቡና፤ሻይና ቅመማቅመም ስትራቴጂያዊ ምርቶች በመሆናቸዉ ከፍተኛ ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራባቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ክልላችን ከተመሠረተ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የተሻሻለ የቡና ዘር አና ፖሊ ባግ ከማቅረብ ባሻገር ተግባሩን ከአሬንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ጋር በማስተሳሰር በበልግና በከረምት ተከላ ወቅቶች እንደየአካባቢዉ ሥነ-ምህዳርና የመልማት አቅም ወቅታዊና ተከታታይ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን ከክትትልና ድጋፍ ሥራዎች ጋር አቀናጅቶ ለመፈጸም ጥረት እየተደረገ ያለ መሆኑን የገለፁት አቶ አስራት ባገባደድነዉ የ2017 በጀት ዓመት 88.5 ሚሊዮን የቡና ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 87.9 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ወይም የዕቅዱን 99 ከመቶ መትከል መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት ከ272 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞችን በመትከል በአራቱም የአመራረት ዘዴዎች ማለትም የጫካ ቡና፤የከፊል ጫካ ቡና፤ የጓሮና ዘመናዊ ተከላ የክልሉን አጠቃላይ የቡና ማሳ ሽፋን ወደ 597,521ሄ/ር ማድረስ ተችሏል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡
የቡና ልማትን ለማስፋፋትና ምርትና ምርታማነት እንድጨምር ለማድረግ እንድሁም ለአየር ንብረት ለዉጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የአሬንጓዴ አሻራ ልማት ሥራ ያለዉ አዎንታዊ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ያብራሩት ዋና ዳይሬክተሩ በክልሉ የሚመረተዉ የቡና ምርት እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዉ ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት በአማካይ ከ52ሺ ቶን በላይ የቡና ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በተያዘው 2018 በጀት ዓመትም የዘርፉን ሥራ ይበልጥ ዉጤታማ ለማድረግ ‹‹ከዕምቅ አቅም ወደ የሚጨበጥ ሀብት›› በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀዉን የክልሉ መንግስት የቀጣይ ሦስት ዓመት የኢንሼትቭ ዕቅድ መሠረት በማድረግ በዘርፉ ከፍ ያለ ዕቅድ በማቀድ ወደ ተግባር የተገባ መሆኑን ያብራሩት ዋና ዳይሬክተሩ በያዝነዉ የከረምት ወራት 30 ሚሊየን 481 ሺህ 724 የቡና ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እስካሀን 18 ሚሊየን 178 ሺህ 450 ችግኝ መትከል መቻሉንና ተግባሩ እስከ ከረምቱ ማብቂያ ድረስ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ አስራት አያይዘዉም አርሶ አደሮቻችንና ቡና አልሚ ባለሀብቶች በቂ የተከላ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ፤ ምንጩ የሚታወቅና ጤናማ የቡና ችግኝ በመጠቀም አሁን ያለዉ የዝናብ ሥርጭት/እርጥበት ሳያልፉ በእጃቸው ያለውን የቡና ችግኝ እንዲተክሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም ቡና የክልላችን ተፈጥሮአዊና እስትራቴጅያዊ ምርት እንደመሆኑ መጠን በክልሉ ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር በማምጣት ረገድ አነስተኛ አግሮ ኢንዱስትሪ እንድስፋፋ እንድሁም ለሴቶችና ወጣቶች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል በሠፊዉ የሚፈጥር በመሆኑ በክልሉ በየደረጃ ያሉ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ተገቢ የሆነ ድጋፍ እንድያደርጉ አቶ አሥራት በድጋሜ ጥር አቅርበዋል፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *