መንግስት የቆዩ የህዝብ ጥያቄዎችን እየመለሰ በመሆኑ መደሰታቸዉን ነዋሪዎች ተናገሩ

Spread the love

ነዎሪቹ ለመንገድ ጥያቄዎች መንግስት በሰጠው ምላሽ መደሰታቸውንና ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል ፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ካሉት አስፋልት መንገዶች አብዛኛዎቹ በጅምር ላይ ያሉ እና በወቅቱ ካለመጠናቀቃቸው የተነሳ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሆነው መቆየታቸዉን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በክልሉ ከሚዛን-ቴፒ፣ከጎሬ-ማሻ-ቴፒ፣ከሺሺንዳ- ቴፒ፣ከጪዳ- ጅማ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተጀምረው በሂደት ላይ ሲሆኑ፦ ከታርጫ- ጪዳ፣ ከዲሪ -ማሻ እና ከቦንጋ ፈለገ-ሠላም-አመያ ግንባታቸዉ ተጀምሮ የተቆሯጡ መንገዶች ናቸዉ።

የተጀመሩትም መንገዶች ባለመጠናቀቃቸው እና የአንዳንዶችም ዉል ተቋርጦ እንደገና ሳይጀመሩ በመቆየታቸዉ በህብረተሰቡ ዘንድ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቷል።

ከእነዚህ መካከል የብልጽግና ፓርቲ እና መንግስት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን በመለየት ወደ ስራ እንዲገቡ በመወሰን በክልሉ የዲሪ ማሻ ምዕራፍ አንድ እና ከታርጫ ጪዳ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ዳግም ወደ ስራ እንዲገቡ በመወሰን ሰኑን በይፋ ስራ እንዲጀምሩ ተደርጓል ፡፡

በእነዚህ የአስፋልት መንገዶች መጀመር ነዋሪዎችም ጥያቄዎቻቸው ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል ፡፡

በካፋ ዞን የጌሻ ወረዳ እና የጊምቦ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ሸዳራሻ ተካልኝ ሽፈራሁ፣ጌሸራሻ አበጀ በሻ እና ወ/ሮ እልፍነሽ ወንድሙ በሰጡት አስተያየት ተጀምሮ የተቋረጠው ዲሪ ማሻ አስፋልት መንገድ በማህበረሱ ዘንድ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል ፡፡

የመንገዱ አለመገንባት ያሰከተለውን ጉዳት ለመንግስት ጥያቄያችንን አቅርበን በመጠባበቅ ላይ እያለን አሁን ላይ ምላሽ መሰጠቱ መሰረታዊ ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱልን በትዕግስት መጠባበቅ እንደሚገባን ምስክር ነው ሲሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ፡፡

በሌላ በኩልም በዳውሮ ዞን ካነጋገርናቸው ነዋሪዎች መካከል መላከ ሀይል አባ ክንፈገብርኤል ገበየሁ፣አቶ ተረፈ ገብሬና ሻምበል አበራ ወ/ጊዮርጊስ በሰጡት አስተያየት የዘመናት ጥያቄያችን በብልጽግና ፓርቲና መንግስት ምላሽ በማግኘቱ ወደፊት ተስፋን እንድንሰንቅ አድርጎናል ሲሉ ተናግረዋል ፡፡

ከታርጫ ጪዳ ያለው አስፋልት መንገድ ተጀምሮ መቋረጡ በትራንስፖርትና መሰል ጉዳዮች በችግር ውስጥ እንድንወድቅ የዳረገን መሰረታዊ ችግራችን ነበር ሲሉም ተናግረዋል ፡፡

አሁን ላይ ለዚህ ጥያቄያችን መንግስት ምላሽ በመስጠቱ በእጅጉ መደሰታቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል ፡፡

ልማቱ የእኛ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ ከመንግስት ጎን በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግና በመተባበር መንገዱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል ፡፡

የብልጽግና ፓርቲና መንግስት የተጀመሩትን የልማት ስራዎች ጨርሶ ማጠናቀቅን በተለያዩ ጊዜያት እያየን የመጣን ሲሆን አሁን የተጀመረውም መንገድ በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ጥርጥር የለንም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ፡፡

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *