የክልሉን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማሻሻል በተሰሩ የማህበራዊ ልማት ስራዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ ተገለጸ።

Spread the love

እየተካሄደ በሚገኘው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት 6ኛ መደበኛ ጉባኤ በምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የአስፈጻሚ ተቋማት ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የክልሉን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማሻሻል በተሰሩ የማህበራዊ ልማት ስራዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የአስፈጻሚ ተቋማት ኃላፊዎች ገልጸዋል።

በክልሉ የነበረውን አጅግ አነስተኛ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግ አጋር አካላትን በማስተባበር ባለፉት ሁለት ዓመታት በተሰራው ስራ ከ350ሺ ህዝብ በላይ የንፁህ መጠጥ ዉሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የገለጹት የክልሉ ውሃ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው በዚህም የክልሉን አማካይ የዉሃ ሽፋን በክልሉ ምሠረታ ወቅት ከነበረበት 32 ከመቶ ወደ 42.8 በመቶ ማድረስ መቻሉን አብራርተዋል።

በመስኖ አውታር ግንባታና አስተዳደር እንዲሁም የማዕድን ሀብት አስተዳደር እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የጠቆሙት ኢንጂነር በየነ በተላይ ከማዕድን ሀብት ቁጥጥርና አስተዳደር ረገድ የታችኛው አስተዳደር አካላት ኃላፊነትን በቁርጠኝነት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በትምህርት ሴክተር ያለውን ስብራት ለመጠገን በተሰራው ስራ የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን የገለጹት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማሀበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አልማው ዘውዴ በዚህም በትምህርት ቤቶች የደረጃ ማሻሻያ ህብረተሰቡን በማስተባበር 1ሺህ 896 አዳዲስ የመማሪያ ክፍል ግንባታ እንዲሁም 1ሺህ 282 ነባር መማሪያ ክፍሎች ጥገና ስራ ከ434 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ የህብረሰብ ተሳትፎ ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር ድጋፍ በክልሉ በቦንጋ ከተማ የሚገነባው የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በቅርቡ የግንባታ ስራው እንደሚጀመር የገለጹት አቶ አልማው በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ለመስጠት የተጀመረው ተግባር በአንዳንድ የክልሉ አከባቢዎች በመምህራን ልማት ዘርፍ ውስንነቶች ቢኖሩበትም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ የህብረተሰብ ተሳትፎውን በማሳደግ የትምህርት ስራውን ውጤታማ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ የገለጹት አቶ አልማው በትምህርት ቤቶች የሚነሳው ‘የብሎክ ግራንት’ በጀት ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም አቅምን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በቀጣይ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በአርብቶአደር አከባቢ ፍትሀዊ የልማት ተደራሽነት ለማዳረስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የክልሉ አርብቶአደርና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ቦኒ የልማት ፍትሀዊነትና ተደራሽነት ለማሳደግ ተጨማሪ ሁለት አዳዲስ የአርብቶአደር ወረዳዎች በፕሮጀክት መታቀፋቸውን ተናግረዋል።

የገበያ ትስስር በመፈጠር አምራቾችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ ከህገወጥ ግብይት ባሻገር በክልሉ እያደገ ከመጣ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በተላይ የነዳጅ እጥረት ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

አልሚ ባለሀብቶችን በማስተባበር በክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች ከ138 ኪሎሜትር በላይ ርዝመት የመንገድ ልማት ስራ ተከናውኗል ብሏል አቶ ተመስገን።

አስፈፃሚ ተቋማቱ በምክር ቤቱ አባላት የተሰጡ ገንቢ አስተያየት ምክረ ሀሳቦች በአዎንታ በመውሰድ በቀጣይ በጀት ዓመት የተሻለ የተግባር አፈጻጸም ለማስመዝገብና የህብረተሰብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *