




የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ዓመታዊ ስብስባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሄዷል።
የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከስብስባው ጎን ለጎን ከዩናይትድ የልማት ሚኒስትር አኔሊስ ዶድስ ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።
አቶ አሕመድ ሽዴ ለልማት ሚኒስትሯ ስለ ማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የመጀመሪያው እና ስኬታማ የፕሮግራም ግምገማ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የሁለትዮሽ አጋሮች የማሻሻያው እርምጃ አካል ለሆነው ለማህበራዊ ጉዳይ የሚውሉ ከፍተኛ ወጪዎችን ዘላቂነት ባለው መልኩ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
የዩናይትድ የልማት ሚኒስትር አኔሊስ ዶድስ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የሪፎርም ጥረቶች አድንቀዋል።
የማሻሻያ ፖሊሲዎቹ ቀረጻ እና ትግበራ በኩል ያለው የፖለቲካ አመራር ሰጪነት እንዲሁም ሪፎርሙ ድሃ ተኮር እና አካታችነትን የተከተለ መሆኑን ገልጸዋል።
በሪፎርሙ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ አየር በመፍጠር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ከማሳደግ አኳያ የተገኙ ጅምር ውጤቶች እና ለውጦች መልካም የሚባሉ ናቸው ብለዋል።
ሚኒስትሯ ኢትዮጵያ ለቀጣናው መረጋጋት የምታበረክተውን ዘላቂ አስተዋጽኦ እንድታጠናክር ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደም ለኢትዮጵያ ልማት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አመልክተዋል።
ሁለቱ ወገኖች ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ያላቸውን ለረጅም ጊዜ የቆየ የሁለትዮሽ ትስስር በከፍተኛ ባለስልጣናት ውይይት ይበልጥ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
አገራቱ ቅድሚያ በሚሰጧቸው ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
