ለበጋ መስኖ ስንዴ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት በስፋት እየተከናወነ ነው – ግብርና ሚኒስቴር

Spread the love

ለ2018 በጀት ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ከ767 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማረስ ከዚህ ውስጥም ከ359 ሺህ ሄከታር መሬት በላይ በዘር መሸፈኑን ገልጿል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የአርሶ አደሩን የስራ ባህል በመቀየር በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ እየተመረተ ይገኛል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ለስንዴ ምርት ልዩ ትኩረት በመስጠት የበጋ መስኖን ጨምሮ የስንዴ ምርትና ምረታማነት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

በግብርና ሚኒስቴር የሰበል ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በ2018 የበጋ መስኖ ስንዴ 4 ነጥብ 29 ሚሊየን ሄክታር መሬት በማረስ 175 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማምረት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።

በዚህ ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ባለፈው ከነበረው ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታሩ ብልጫ እንዳለውም ገልጸዋል።

በዘንድሮው የበጋ መስኖ ስንዴ እስከ አሁን ከ767 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በማረስ ከ359 ሺህ ሄከታር መሬት በላይ በዘር መሸፈኑን ጠቁመዋል።

በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ በበጋ መስኖ ስንዴ የተገኘውን ልምድ የበለጠ በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚያሰችል መልኩ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘርና የውሃ ፓምፕ አቅርቦት ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል።

ከአፈር ማዳበሪያ ጋር ተያይዞ ከመኸር ምርት የተረፈ እና ለመስኖ የተዘጋጀ ለአርሶ አደሮች መከፋፈሉን የስንዴ ምርጥ ዘርም በበቂ ሁኔታ ለበጋ መስኖ ስንዴ ተደራሽ መደረጉን ገለጸዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ከዓመት ወደ ዓመት ትልቅ እርምታ እያስመዘገበ መምጣቱን ተናግረዋል።

ስንዴ በምግብ ምርት እራስን ከመቻል ጋር የተያይዘና እንደ ሀገር የተጀመረው ስኬት ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ የተያዘው ግብ እንዲሳካ የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትላቸውን እንዲያጠናከሩም ጥሪ አቅርቧል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *