



አዲስ አበባ፤ሕዳር 23/2018 (ኢዜአ)፡-ከለውጡ መንግሥት በኋላ የግብርናው ዘርፍ አስደናቂ ለውጥ ማምጣቱን የሶማሌ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አሕመድኑር አብዲ ለኢዜአ እንዳሉት፤ እንደ ክልል ከለውጡ መንግሥት በፊት ሲታረስ የነበረው መሬት 389 ሺህ 949 ሔክታር ነው።
የለውጡ መንግሥት ለክልሉ በሰጠው ልዩ ትኩረት በአሁኑ ወቅት 1 ሚሊየን 585 ሺህ 889 ሔክታር መሬት እየለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህ የለውጡ መንግሥት ትጋት ቀደም ሲል ክልሉ ለአርብቶ አደር እንጅ ለግብርና ሥራ እንደማይሆን የተተከለውን ትርክት በተግባር ያፈረሰ ነው ብለዋል።
በዚህ ሂደትም አሁን ላይ እንደ ክልል 971 ሺህ 430 አባዎራዎችን በግብርና ልማት ብቻ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው ያነሱት።
ምንም እንኳን እንደ ሰብሉ ዓይነት ቢለያይም በአሁኑ ወቅት በአማካይ በሔክታር 40 ኩንታል እንደሚመረት ጠቁመዋል።
መልማት የሚችል መሬት እያለን በሚፈለገው ልክ በማልማት ተጠቃሚ ሳንሆን መቆየታችን ቢያስቆጭም፤ አሁን ማካካስ ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል።
የለውጡ መንግሥት በቅድሚያ የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ መቻሉ እና ሕዝቡ ተረጋግቶ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር በማድረጉ ሰፊ መሬት ለማልማት ተችሏል ነው ያሉት።
ከአርብቶ አደርነት ጎን ለጎን የእርሻ ሥራዎችንም በስፋት በማከናወን ሕዝቡን በይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ መሠራቱ የሚለማውን መሬት መጠን እንዳሳደገው ተናግረዋል።
