ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች አስፈጻሚ አካላት ምላሽ ሰጡ።

Spread the love

በ6ኛው ዙር 3ኛ ዓመት 5ኛ መደበኛ ጉባኤ በቀረበው የአስፈጻሚ አካላት ሪፖርት ላይ የምክርቤት አባላት ላነሱት ጥያቄዎች የክልሉ አስፈፃሚ አካላት ምላሽ ሰጥተዋል።

በግብርና ስራዎች ዙሪያ ለተነሱ ጉዳዮች ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ ማስረሻ በላቸው በሰጡት ማብራሪያ የሌማት ትሩፋት ስራዎችን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ህብረተሰቡን በመንደር በማደራጀት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

በአገዳ ሰብሎች የምርጥ ዘር አቅርቦት ባለፉት 6 ወራት 38 ከመቶ መሰራጨቱን ገልጸው ይህም በስፋት በቀጣይ የበልግ ወቅት እንደሚሰራ አብራርተዋል ።

በክልሉ የሚስተዋለውን የድህረ ምርት ብክነት ለመከላከል ስትራቴጂካዊ አሰራሮችን በመከተል በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የግብርና መካናይዜሽን ስራዎችን አጠናክሮ ከመሄድ አንጻር ከ46 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መሰራቱን ያብራሩት አቶ ማስረሻ በላቸው በቀጣይ አጠናክሮ ይሰራል ብለዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በክልሉ የ8ኛ እና የ6ኛ ክፍል ፈተናዎችን ለማዘጋጀት ጥረቶች ተደርገዋል ብለዋል።

የክልሉ መንግስት የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና አዘጋጅቶ ተግባራዊ ማድረጉንና የ6ኛ ክፍል ፈተናን በተመለከተ የሰው ኃይል እና በጀት ዕጥረት በመኖሩ በዞኖች እንዲሸፈን ተደርጓል ብለዋል።

የመምህራን ልማት ስራዎችን በተመለከተ ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት በቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ ከ500 በላይ ዕጩ መምህራን በድግሪ መርሃ ግብር እየሰለጠኑ መሆኑን ተናግረዋል ።

የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም በሰጡት ማብራሪያ በክልሉ የወባ በሽታ ወረርሽኝን ለመከላከል ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

ለዚህም የጤና ሚኒስቴር እና የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል በህብረተሰቡ ዘንድ የአጎበር አጠቃቀም ክፍተቶችን ማስተካከልና ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ውሃ አቋሪ ቦታዎችን የማፋሰሱ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመንግስት የጤና ተቋማት ብቻ መገኘት የሚገባቸው እንደኳርተም የመሳሰሉት መድኃኒቶች በግል የጤና ተቋም በስፋት በመገኘታቸውም ይህንን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ 16 ተቋማት ታሽገው ለህግ የማቅረብ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ በምላሻቸው አብራርተዋል ።

የአምቡላንስ አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተም ኮንታ ዞን የተሻለ መሆኑን በመግለጽ ሌሎች ዞኖች በልዩ ትኩረት ወደ ተግባር እንደመገቡ ጠይቀዋል።

ከቀድሞ ደቡብ ክልል ከ60 በላይ አዳሪ የጤና ፕሮጀክቶችን ተቀብለን ደረጃ በደረጃ ለማስጨረስ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ህብረተሰቡ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ለፍጻሜ ማብቃት ይጠበቅብናል ብለዋል አቶ ኢብራሂም።

ከማዕጠመ አንጻር መሻሻሎች ቢኖሩም የአመራር ድጋፍ በልዩ ሁኔታ ትኩረት የሚሻ መሆኑን አቶ ኢብራሂም ተናግረዋል ።

ለጤና ተቋማት በጀት ያልመደቡ እና አንዳንዶቹ ደግሞ ከመቶ ሺህ ያነሰ በጀት መመደብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት አዳጋች እየሆኑ መምጣታቸውና የምክርቤት አባላትም ዕገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል ።

ከንጹህ መጠጥ ውሃ አኳያ አብዛኛው ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ በመሆናቸው አንዳንድ የውሃ ተቋማት በተያዘላቸው ጊዜ ሊጠናቀቁ አለመቻላቸው፣ የኮንትራክተሮች አቅም ማነስና የሚዋዥቅ የገበያ ሁኔታ መሠረታዊ ችግሮች መሆናቸውን የውሃ፣ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው አብራርተዋል።

የሚዛን አማን ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ ጥናትና ዲዛይን ተሰርቶ ለውሃና ማዕድን ሚኒስቴር መረጃው ተልኳል ብለዋል።

የቦንጋ ከተማ ንጹህ መጠጥ ውሃ ችግርን ለመቅረፍ በአጭር፣በመካከለኛ በረጂም ጊዜ የሚሰሩ ተግባራት ተለይተው እየተሰሩ ይገኛል ብለዋል።

በቅርቡም 13 ሺህ የከተማዋ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የማድረግ ስራ መሰራቱንና ሌሎች ስራዎችን በሂደት ለመመለስ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል ኢንጂነር በየነ።

በገሳ ጭሬ በቀድሞ ክልል የተጀመረ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ አፈጻጸሙ 85 በመቶ የደረሰ መሆኑንና የፓምፕና የጀነሬተር መግጠም ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *