ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በዩጋንዳ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው

Spread the love

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በዩጋንዳ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ጉብኝቱ እየተካሔደ ያለው በዩጋንዳ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም እና የፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የመጀመሪያ ልጅ በሆኑት ጄኔራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ በተደረገላቸው ግብዣ መሰረት ነው፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ እና የልዑካን ቡድናቸው ዩጋንዳ ኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱም በዩጋንዳ ምድር ኃይል ኮማንደር ሌተናል ጄኔራል ካያንጃ ሙሃንጋ፣ በዩጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር እፀገነት በዛብህ ይመኑ እና በሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ፊልድ ማርሻሉ ከዩጋንዳ ህዝብ መከላከያ ሠራዊት ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ሙሃዚ ኬይነሩጋባ ጋር ሁለቱ ሀገራት በመከላከያ ዘርፍ ባላቸው ትብብር ዙሪያና የቀጣናውን ሰለምና ፀጥታ በማስፈን ረገድ እያደረጉት ያለውን ሚና አጠናክረው ለማስቀጠል በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ምክክር አድርገዋል፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያ ከዩጋንዳ ጋር ያላት ግንኙነት ስትራቴጂክ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከተጠናከረው የሁለትዮሽ ግንኙነት በተጨማሪ በቀጣናው ሰላምና ጸጥታን በማስፈን ረገድ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የዩጋንዳ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሙሆዚ ካይኔሩጋባ፤ ለፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላና ለልዑካን ቡድኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን በማስቀደም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ከአክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮ በታሪክና በደም የተሳሰረና አሁንም የተጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይቱም ሁለቱ ሀገራት በተናጠልም ሆነ በጋራ የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የተሻለ አስተዋፅኦ ለማበርከት የሚቻልበት ሁኔታ የተዳሰሰ ሲሆን በአቅም ግንባታና ተጨማሪ ትብብሮችን አስመልክቶ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ለማድረግ ትኩረት ሰጥተው ከስምምነት ላይ መድርሳቸው ተገልጿል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በነገው እለትም በተያዘው ፕሮግራም መሠረት ከዩጋንዳ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *