




የሸካ ዞን ጤና መምሪያ የ2017 የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ተግባር ያለበት ደረጃና የቀጣይ ተግባራት ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቴፒ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
የውይይት መድረኩን የመሩት የሸካ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ በላቸው ጋራ እንደተናገሩት የወባ ስርጭትን መከላከልና መቆጣጠር ስራ የሁሉንም ህብረተሰብ ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።
በየደረጃው የሚገኘው የፓርቲና የመንግስት አመራር
ክረምት መግባትን ተከትሎ የወባ ስርጭት ከፍ እያለ በመሆኑ ህብረተሰቡን በማስተባበር የመከላከልና መቆጣጠር ዘመቻው ላይ ሁሉም ልረባረብ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል አቶ በላቸው።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወሰን ጨመሰ እንደተናገሩት በሸካ ዞን የወባ ስርጭትን ለመከላከልና መቆጣጠር እየተደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተው ስርጭቱን ለመግታት በቅንጅት ይሠራልም ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያሻሽሉ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት በማጠናከር በዘርፉ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን መፍታት ያስፈልጋልም ሲሉ በአፅንኦት አንስተዋል።
ከወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ጎን ለጎን አጠቃላይ የጤና ዘርፍ ተግባራት በተቀናጀ መልኩ መመራት አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
የሸካ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ እምሩ ወዬሳ የዞኑን የ2017 ዓ.ም የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ተግባር ያለበት ደረጃና የቀጣይ ተግባራት ዕቅድ ያቀረቡ ሲሆን ባለፈው በጀት ዓመት በወባ መከላከልና መቆጣጠር ዘመቻው የተገኙ ስኬቶችንና ያጋጠሙ ማነቆዎችን በዝርዝር አንስተዋል።
ውጤታማ የአካባቢ ቁጥጥር ያለመኖር ፣የማፋሰስና ማዳፈን ስራ በሚፈለገው ደረጃ ያለመሆን፣የአልጋ አጎበር አጠቃቀም እና የአጎበር ተደራሽነት ውስንነት መኖርና ሌሎችም ጉዳዮች እስካሁን ባለው የወባ ስርጭትን ለመግታት ማነቆ መሆናቸውን አብራርተዋል አቶ እምሩ።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው የወባ መከላከልና መቆጣጠር ዘመቻ የጤና ዘርፍ ተግባር ብቻ ባለመሆኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።
ዘመቻውን ስኬታማ በሆነ መልኩ በመምራትና በማስተባበር ስርጭቱን ለመግታት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡም አረጋግጠዋል ተሳታፊዎቹ።
የወባ በሽታን መከላከልና መቆጣጠር ዘመቻን ጨምሮ በአጠቃላይ የጤና ዘርፍ ተግባራትን ውጤታማ ለማድረግ ጠንካራ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉና ከዞኑ ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩ የገለፁት ደግሞ ከክልሉ ጤና ቢሮ የተመደቡ አመራሮችና ባለሙያዎች ናቸው።
በመድረኩ የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወሰን ጨመሰን ጨምሮ የክልሉ ጤና ቢሮ ከፍተኛ ባለሙያዎች፣የሸካ ዞን የመንግስትና የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም የዞኑ ጤና መምሪያ ማኔጅመንት አባላት ተሳትፈዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
