የተለያዩ ሀሰተኛ ሰነዶችን በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ያዘጋጅ የነበረን ርዕሰ መምህር ከግብረአበሩ መምህር ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሸካ ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

Spread the love

በሸካ ዞን ፖሊስ መምሪያ የፎረንስክ ምርመራ ዲቭዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ተግባሩ ክፍሌ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነትና ኮሜንኬሽን እንደገለፁት በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ሐምሌ 08 ቀን 2017 ዓ.ም ሰዓቱ ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት በቴፒ ከተማ ሰላም ቀበሌ ልዩ ስሙ ሳይሌንት ፔንሲዮን ተብሎ በሚጠራ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚሰሩና የሚያሰራጩ መምህራን መኖራቸውን ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ሁለት መምህራን በቁጥጥር ስር ሊውሉ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

ተጠርጣሪዋቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሊውል የቻሉት አንዲት ግለሰብ የትምህርት ማስረጃ ከ10ኛ ክፍል ወደ 11 ክፍል እንደተዛወረች በማስመሰል ሀሰተኛ ማስረጃ በመስጠታቸውና ወደ አንድ መንግስታዊ ተቋም ለመቀጠር ስትሄድ ጥርጣሬ ውስጥ በመግባታቸው ለፖሊስ መረጃውን በመስጠታቸው እንደሆነ ኢንስፔክተር ተግባሩ ገልፀዋል፡፡

አክለውም ግለሰቧ ከተቋሙ የልደት ሰርተፊኬት እንድታመጣ ስትጠየቅ ሁለቱ ግለሰቦች ጋር በመሄድ ሀሰተኛ የልደት ሰረተፊኬት በማምጣት አንደኛው ርዕሰ መምህር ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀትና ሁለተኛው መምህር በአገኛኝነት ከግለሰቧ1000 ብር ተቀብሎ ለርዕሰ መምህሩ 600 ብር ለራሱ 400 ብር የተከፋፈሉ መሆኑን በምርመራ መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡

የሸካ ዞን ፖሊስ ከቴፒ ከተማ ፖሊስ ጋር ባደረገው ክትትል አንደኛው ተጠርጣሪ የአንድ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር መኖሪያ ቤት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በተደረገው ብርበራ ክብ ማተሞች 5፤የራስጌ ማህተሞች ብዛት 5፤የተለያዩ ኃላፊዎች የስምና የስራ ኃላፊነት ቲተሮች ብዛት 5፤የ1ኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማህተሞች፤የነርሲግ፤የአካውንቲን የዲፕሎማ የትምህርት ማስረጃዎች እና የልደት ሰርተፊኬቶች ከመኖሪያ ቤቱ ሊገኙ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የሸካ ዞን ፖሊስ የምርመራ ቡድን በማዋቀር ምርመራውን በስፋትና በጥራት እያከናወነ መሆኑን ኢንስፔክተር ተግባሩ ጠቁመዋል፡፡የሸካ ዞን ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ዲቭዥን ኃላፊ ኮማንደር ልሳነወርቅ ተስፋዬ በጉዳዩ ዙሪያ ጠይቀናቸው የሁለቱ ግለሰቦች ድርጊት ሌሉች ሙያቸውን አክብሮ የሚሰሩ መምህራንን እንደማይወክል ተናግረዋል፡፡

አክለውም ህብረተሰቡ በሀሰተኛ ትምህርት ማስረጃ ከመጠቀም እንዲቆጠብና ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ እየተበራከተ መምጣቱንና ህብረተሰቡ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚያዘጋጁትን ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪያቸውን አቅርበዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዘግቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *