በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል በተሟላ ሁኔታ ለማቅረብ የባለድርሻ ተቋማት ትብብር ማጠናከር ይገባል- ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር)

Spread the love

በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል በተሟላ ሁኔታ ለማቅረብ የባለድርሻ ተቋማት ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኮርፖሬሽኑ አመራሮች ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ በልዩ የኢኮኖሚ ዞን ያለውን የኃይል አቅርቦት በተሟላ ሁኔታ ማቅረብ በሚቻልባቸው ሁኔታ እና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በፍጥነት ለመፍታት ያለመ ውይይት ተካሄዷል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሰሃ ይታገሱ (ዶ/ር) በልዩ ኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገቡ ባለሃብቶች ስራቸውን በስኬት ለመከወንና ወደ ዞኖቹ ለመግባትም የኃይል አቅርቦት ጉዳይ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ከሁለቱ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፥ ተግዳሮቶች ሲያጋጥሙም ደግሞ በፍጥነት መልስ መስጠት መቻሉ የሚበረታታና ትብብሩን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በበኩላቸው ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመላው ሃገሪቱ በሚገኙት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና በድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና የኃይል አቅርቦቱን በተሟላ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ወደፊትም የሃገርን ልማት ለማረጋገጥ በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡

በልዩ የኢኮኖሚ ዞን በተሟላ ሁኔታ አቅርቦቱን ለማቅረብና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በፍጥነትና በጥራት ለማከናወን የሚያስችል ከሶስቱ ተቋማት የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሯል።

ኮሚቴው በቀጣይም ስራዎችን በጋራ በመስራት ችግሮች ሲያጋጥሙ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚያስችል ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *