የባሕር በር ጥያቄ የውስጥ ልዩነቶችን የሚሻገር የትውልድ ጥያቄ ነው

Spread the love

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ የውስጥ ልዩነቶችን የሚሻገር የትውልድ ጥያቄ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው የ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ፣ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው።

ከምክር ቤት አባላቱ ለሚኒስትሩ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል፤ ኢትዮጵያ በታሪካዊ ስህተትና ግፍ የተነፈገችውን የባሕር በር ለማስመለስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምን እየሠራ እንደሆነና ከዜጎች ምን ይጠበቃል የሚሉት በዋናነት ተነስተዋል።

ሚኒስትሩ ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ የባሕር በር ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስከብር መልኩ በስፋት እየተሠራበት መሆኑን ገልጸዋል። እስካሁንም የኢትዮጵያ ጥያቄ እና የፍላጎቷ ምንነት ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በግልጽ ማስረዳት መቻሉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን ፍላጎት የማስገንዘቡ ሥራ ውጤት ማስገኘቱን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ጥያቄው እንዴት ይመለስ? ወደሚለው ተግባራዊ ምዕራፍ መሸጋገሩን አብራርተዋል።

የባሕር በር የአንድ ፓርቲ፣ የወገን ወይም የግለሰብ ጥያቄ ሳይሆን የሀገርን ዘላቂ ጥቅም የሚያረጋግጥና የውስጥ ልዩነቶችን የሚሻገር የትውልድ ጥያቄ በመሆኑ፤ ጥያቄው ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ሁሉም ዜጋ ያለልዩነት በአንድነት ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይም የኢትዮጵያን መዳከምና መኮስመን ለሚመኙና ለዚህም ሌት ተቀን ለሚሠሩ አካላት መጠቀሚያ ላለመሆን ሁሉም ዜጋ በተጠንቀቅ ሊቆም እንደሚገባ ሚኒስትሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *